News Detail

National News
Jan 29, 2024 736 views

የከፍተኛ ትምህርት የተማሪዎች የወጪ መጋራት ክፍያን በማስፈጸም ረገድ ክፍተት መኖሩ ተገለጸ

በከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ወጪ መጋራት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
 
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የአስተዳደርና መሠረተ-ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሰለሞን አብረሃ በባለድርሻ አካላት የእርስ በርስ መናበብና መቀናጀት ከፍተት የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች የወጪ መጋራት ክፍያ በአግባቡ እየተሰበሰበ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
 
የተማሪዎችን የወጪ መጋራት ክፍያን በወቅቱ ተከታትለው የሚያስፈጽሙ ተቋማት ቢኖሩም በርካታ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በተዘረጋው የአሠራር ሥርዓት መሠረት ክፍያውን ተከታትለው በማስፈጸም ረገድ ክፍተት እንደሚታይባቸው ዶ/ር ሰለሞን ገልጸዋል።
 
በመሆኑም የመንግሥት ገንዘብ በአግባቡ ተሰብስቦ ለተመሳሳይ ዓላማ ጥቅም ላይ እንዲውል ተቋማትና ባለድርሻ አካላት በቅንጅትና በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ መሪ ሥራ አስፈጻሚው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የአስተዳደር ጉዳዮች ዴስክ ኃላፊ አቶ አብዶ ናስር በበኩላቸው የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች የወጪ መጋራት ክፍያ መከፈል በሚገባው ወቅት አለመከፈሉ የመንግስትን ተጨማሪ የኢንቨስትመንት አቅም የሚገድብ መሆኑን ጠቅሰው ተማሪዎችም የተጋሩትን ወጪ በሚጠበቅባቸው ወቅት ካልከፈሉ ለተጨማሪ የወለድ ክፍያም ሆነ ተሰብሳቢ እዳ የሚጋለጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
 
አቶ አብዶ አክለውም ይህንን ችግር ከመሰረቱ ለመቅረፍ ትምህርት ሚኒስቴር በአሰራር፣በመረጃ ጥራትና በክትትል ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው ጉዳዩ የሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላትም የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
 
በውይይት መድረኩ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ከመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከገቢዎች ሚኒስቴር ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ተገኝተዋል፡፡
Recent News
Follow Us