News Detail
ትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት የሚያስችል አደረጃጀትን ይፋ አደረገ፡፡
በውይይቱ ላይ ከትምህርት ቤት እስከ ፌደራል ድረስ የትምህርት አከፋፈትን የሚመሩ አራት አደረጃጀቶች መዋቀራቸው ይፋ ተደርጓል ፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ ትምህርት ቤቶችን ዳግም ለመክፈት ከትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ፌደራል ድረስ ሊኖር ስለሚችለው አደረጃጀት እና ስለሚያከናውኑት ተግባርና ሃላፊነት ሰነድ አቅርበዋል፡፡
አደረጃጀቱም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ የየክልል ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም የወረዳ አስተዳዳሪዎች በበላይነት እንደሚመሩት እና የወላጅ ኮሚቴዎች በስፋት የሚሳተፉበት መሆኑም ተገልጿል፡፡
ሚኒስትሩ እነዚህ ከትምህርት ቤት እስከ ፌዴራል ድረስ የተቋቋሙት አደረጃጀት በሀገራችን ባሉ ትምህርት ቤቶች የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት መኖሩን፣ ግብዓቶች መሟላታቸውን በማረጋገጥ ትምህርት እንዲጀመር የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡
የተዋቀረው አደረጃጀት የትኛውም ትምህርት ቤት ኮቪድን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችንና ግብዓቶችን ማሟላቱን እስካለረጋገጠ ድረስ ትምህርት ቤቶች እንማይከፈቱ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር በሀገራችን ትምህርት በሦስት ዙር እንዲጀመር በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ መሰረት የተለያዩ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ ግብዓቶችን እያሰባሰበ እንደሚገኝም በመድረኩ መገለፁን የኮሚዬኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዘግቧል።