News Detail
Oct 21, 2025
41 views
በኢትዮጵያና በቻይና መንግስታት መካከል በትምህርት መስክ ያለው የትብብር ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱ ተገለጸ፤ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ከቻይናዋ ሻንዢ ግዛት የልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሹኔ ከቻይናዋ ሻንዢ ግዛት ምክትል ገዢ ዋንግ ዢአዎ የተመራ ልዑካን ቡድን ባነጋገሩበት ወቅት እንደገለጹት በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ የትብብር ግንኙነት መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የትብብር ግንኙነት በአሁኑ ጊዜ ወደ ስትራጂካው አጋርነት መሸጋገሩንም ክቡር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡
የቻይና የስልጣኔ ማዕከል የሆነችው የሻንዢ ግዛት ከኢትዮጵያ ጋር በባቡር ፣ በቴክኒክና ሙያ እና በሌሎችም መስኮች የትብብር ግንኙነት እንዳላትና ትምህርት ሚኒስቴር ከግዛቲቱ ጋር ያለውን ትብብር በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍም ማጠናከር እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በርካታ ዩኒቨርስቲዎች መገንባታቸውንና በአሁኑ ወቅት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጥራት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ግዛቲቱ በሳይንስ ፣ በቴክኖሎጂና በሌሎችም መስኮች ያላትን ልምድና ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በግብርና ምርምር ፣ በኢኖቬሽን፣ በትምህርትና በአቅም ግንባታ መስኮች በትብብር በመሰራት ግዛቲቱ ከጅማ ዩኒቨርስቲ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢየ ስምምነት በአርአያነት የሚታይ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ቻይናዋ ሻንዢ ግዛት ምክትል ገዢ ሚስተር ዋንግ ዚአዎ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ቻይና ዘርፈ ብዙ ስትራቴጂካዊ አጋሮችና ወዳጆች መሆናቸውን ገልጸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት በቻይና አፍሪካ ግንኙነትም በግንባር ቀደምነት የሚታይና በማደግ ላይ ላሉ አገራትም በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በሻንዢ ግዛት በኢትዮጵያ በትምህርት መስኩ በተለይም በነጻ የትምህርት እድል ፣ በምርምር፣ በኢንጂነሪንግ ፣ በእርሻ ፣ በህብረተሰብ ጤና እና በሌሎችም የትብብርመስኮች ያለውን ግንኙነት ማጠናከርና ማስቀጠል እንደምትፈልግም አስታውቀዋል።
በዚህ ዓመትም በግዛቲቱ ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች 5 ነጻ የትምህርት እድል ለመስተት ዝግጁ መሆኗንም የቻይናዋ ሻንዢ ግዛት ምክትል ገዢ ሚስተር ዋንግ ዚአዎ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም የጅማ ዩኒቨርስቲ ፕሩዚዳንት ጀማል አባ ፊጣ (ዶ/ር) እና በቻይና የያንግሊንግ አግሪካልቸራል ሃይ-ቴክ ኢንደስትሪያል ዲሞንስትሬሽን ዞን (Agricultural High-Tech Industrial Demonstration Zone, China) ምክትል ጸሀፊ ሚስተር ዋንግ ጁን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።