News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Sep 02, 2025 107 views

የምርምርና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደገበያ የማስገባት ተግባር የሪፎርም አካል ተደርጎ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑ ተገለጸ።

ለዩኒቨርሲቲ እንዱስትሪ ትስስር ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተሮችና የኢንኩቤሽን ማዕከላት አስተባባሪዎች ስልጠና ተሰጥቷል።
የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ፣ የምርምር እና ማህበረሰብ ጉድኝት መሪ ስራ አስፈጻሚ ሰራዊት ሃንዲሶ (ዶ/ር) በስልጠናው ላይ እንደገለጹት የምርምርና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደገበያ የማስገባት ሥራ በአገር አቀፍ ደረጃ እንደዋና ዕቅድ ተይዞ እየተሰራበት ይገኛል።
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተቋቋሙ 27 የኢንኩቤሽን ማዕከላትን የማጠናከርና ያላቋቋሙትም እንዲያቋቁሙ እየተደረገ መሆኑንም ዶ/ር ሠራዊት ተናግረዋል።
የኢንኩቤሽን ማዕከላት ማቋቋም የሥራ አጥነትን ችግር በማቃለል፣ የተግባር ልምምድ ለማድረግ በተለይም ክህሎትና ሥራ ፈጠራ ችግሮች ለመቅረፍ እንደሚያስችልም መሪ ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
የኢንኩቤሽን ማዕከላትን ማስፋፋት በተለያዩ የትምህርት መስኮች መካከል ሊኖር የሚችለውን መስተጋብርና ቅንጅት የተሻለ በማድረግ ፈጠራና የሳይንስ ዕውቀት እንዲዳብር ለማድረግ እንደሚያግዝም ዶ/ር ሠራዊት ጨምረው አስረድተዋል።
የተቋማት ትስስር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዴስክ ኃላፊ አቶ ተሾመ ዳንኤል በበኩለቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወደ ራስ ገዝነት በሚያመሩበት ወቅት በፋይናንስ ራስን የመቻል ሂደትን የሚደግፉ ተግባራትን ማከናወን ቅድምያ የሚሰጠው አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ እውን እንዲሆን የአዕምሯዊ ንብረትን፣ ቴክኖሎጂን እና የምርምር ውጤቶችን ወደ ገበያ በማስገብት ፤ የኢንኩቤሽን ማዕከላት ጥምረት መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡
የሚሸጋገሩ የፈጠራ እና የቴክኖሎፐጂ ውጤቶች ተጽኖ መገምገም በሚያስችል ዲጂታል ፕላትፎረም የተደገፈ ስርዓት መዘርጋትና በፈጠራ ሀሳብ ላይ መዋለንዋያቸውን ማፍሰስ ለሚፈልጉ ኢንዱስትሪዎች ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርላቸው አቶ ተሾመ አስገንዝበዋል፡፡
በትስስር አዋጅ 1298/2015 ማስፈጸሚያ መመሪያዎች፣ የምርምር እና ተክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ ገበያ የመስገባት ሂደት እና የቢዝነስን፣ ፈጠራ እና የቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ማዕከላት አስተዳደር ዙሪያ ባተኮረው ስልጠና የዩኒቨርሲቲ እንዱስትሪ ትስስር ፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተሮችና የኢንኩቤሽን ማዕከላት አስተባባሪዎች ተሳትፈዋል።
Recent News
Follow Us