News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Aug 29, 2025 83 views

ትምህርት ሚኒስቴር ከቻይና ህዝባዊ ሪፐብሊክ ትምህርት ሚኒስቴር አለም አቀፍ የህዝብ ለህዝብ ልውውጥ ማዕከል ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ሠነድ ተፈራረመ።

ትምህርት ሚኒስቴር ከቻይና ህዝባዊ ሪፐብሊክ ትምህርት ሚኒስቴር አለም አቀፍ የህዝብ ለህዝብ ልውውጥ ማዕከል ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ሠነድ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ የተቋም ለተቋም ግንኙነትን በማጠናከር የሁለቱ ሀገራት የእውቀትና ክህሎት ሽግግርን ለማሳለጥ የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል።
የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚንስትር ድኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሹኔ ስምምነቱን በፈረሙበት ወቅት የቻይና መንግስት በኢትዬጵያ የትምህርት ልማት ዘርፍ ውስጥ ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል
ሚኒስትር ድኤታው በማያያዝም ስምምነቱ ሀገራዊ ፍላጎት ላይ መሠረት በማድረግ በተለይም በማደግና በመስፋፋት ላይ ያሉ የዲጂታል፣ ሠው ሠራሽ አስተውሎ ፣ ሳይበር ሴኪዩሪቲና መሠል ትብብሮች ላይ የቻይና ባለሙያዎችንና ተቋማትን ድጋፍ እንደሚሹ አስገንዝበዋል።
መሠል ትብብሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን በማጠናከርና ቅርርቦሽን በመፍጠር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን አጋርነትና ትብብር በበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን ሚንስትር ድኤታው በማያያዝ ገልጸዋል።
የቻይና ህዝባዊ ሪፐብሊክ ትምህርት ሚኒስቴር አለም አቀፍ የህዝብ ለህዝብ ማዕከል ሀላፊ ዩ ቻንግሺዩ በበኩላቸው ቻይና አሁን ለደረሠችበት የእድገት ደረጃ የአለም አቀፍ ትብብር ያለው ሚና ወሳኝ መሆኑን ትገነዘባለች ያሉ ሲሆን በትምህርትና ተያያዥ ልውውጦች ከኢትዮጵያ ጋር ተባብሮ ለመስራት ፍላጎት ያላት መሆኑን ገልጸዋል።
እንደዚህ ዓይነት ትብብሮች መጪው ትውልድ በሀገራቱ መካከል ያለውን ትብብርና ጠንካራ ወዳጅነት አብዝቶ እንዲረዳ መሠረት የሚጥል በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የማዕከል ሀላፊው አስገንዝበዋል።
Recent News
Follow Us