News Detail
Apr 02, 2025
112 views
የአገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት መሰረትና ደጋፊ ለሆነው የትምህርት ዘርፍ ውጤታማነት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ፤
“ትናንት፣ ዛሬና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል ርዕስ ባለፉት ሰባት ዓመታት የለውጥ ስኬቶች ዙሪያ የትምህርት ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞች ውይይት አካሂደዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ውይይቱን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት የትምህርት ዘርፉ የአገሪቱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ እድገት መሰረት በመሆኑ በቁጭትና በእልህ በመስራት የሚፈለገው ለውጥ እንዲመጣ መረባረብ ይገባል፡፡
በአገሪቱ ባለፉት ሰባት አመታት በለውጥ ጊዜ የሚጠበቁ በርካታ ተግዳሮቶች የገጠሙና አሁንም ያለተሻገርናቸው ፈተናዎች ቢኖሩም የትምህርት ዘርፉን ጨምሮ በየዘርፉ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን አስረድተዋል፡፡
የለውጡ ጊዜ ማህበራዊ ሚዲያ ቀውስ የነገሰበት ፣ በዓለማችን አዲስ ስርዓት እተወለደ ያለበትና ልዩ ልዩ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች የተዛቡበት እና አስቸጋሪ ወቅት መሆኑንም ክቡር ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም ችግሮችና ፈተናዎችን በጽናት በመቋቋም በቁጭት መስራትና አገሪቱንም ከእርዳታ ጠባቂነትና ከኋላ ቀርነት ማላቀቅና የህዝቦቿን ክብርና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ዘላቂ ሰላምና ዴሞክራሲን ለማስፈን እና ከአድልዎ የጸዳ መንግስታዊ ስርዓትና መዋቅር መገንባት ወሳኝ መሆኑንም ክቡር ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ አስገንዝበዋል፡፡
የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከርና ከጎረቤት አገራት ጋር በመሰረተ ልማት በመተሳሰር የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሹኔ በበኩላቸው የምንሰጠው ትምህርት ወቅቱ ከደረሰበት የቴክኖሎጂ እድገት ጋር ሊያራምድ የሚችል መሆኑን እየፈተሹና እያረጋገጡ መሄድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በመድረኩ “ትናንንት፣ ዛሬና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል ርዕስ ባለፉት ሰባት ዓመታት በተመዘገቡ የለውጥ ስኬቶች ዙሪያ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
Recent News
የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራም ብቃት ማዕቀፍ ለትግበራ መሆኑ ተገለጸ፤
Mar 14, 2025
የትምህርት ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ጋር ተወያዩ፤
Mar 14, 2025