News Detail
የሀገር ውስጥ ዜና
Mar 14, 2025
196 views
የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች ብቃትና ጥራት ያላቸውን መምህራን ማፍራት እንዲችሉ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።
የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች የማሰልጠን አቅማቸውን ለማሳደግ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።
በመድረኩም የመምህራን ስልጠና ከአጀማመሩ ጀምሮ እስካሁን የሄደባቸው መንገዶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለውይይት መነሻ ፅሁፍ ቀርቧል።
በዚሁ ጊዜ የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ተዋናዩ ብዙ ቢሆንም መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ድርሻ ትልቅ መሆኑን ጠቁመው የዚህ መድረክ አላማም በመምህራን ስልጠና ያሉ ተግዳሮቶችን ነቅሶ በማውጣት የጋራ መግባባት በመፍጠር ሥራዎችን በውጤታማነት መስራት ማስቻል መሆኑም ገልጸዋል።
አክለውም ፍትሃዊና ጥራት ያለው ትምህርትን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የመምህራንን አቅም ማሳደግ ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሙሉቀን ንጋቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት የመምህራን ስልጠና ሥርዓትን ለማሻሻል የተለያዩ ዘዴዎች ተዘርግተው ተግባራዊ ቢደረጉም ችግሩን በመሠረታዊነት ሊፈቱ አልቻሉም ያሉ ሲሆን፣
አሁን እነዚህን ተግዳሮቶች በማስተካከል ብቃትና ጥራት ያላቸው መምህራንን ለማፍራት እንዲቻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አክለውም በስራ ላይ ያሉ መምህራንን አቅም ለማሻሻልም ልዩ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተዘጋጅቶ እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
በመድረኩም መምህራንን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል እና ሌሎች እጩ ሰልጣኞች ሙያውን ወደው እንዲመጡ የሚያስችሉ የተለያዩ የማበረታቻ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባም ተጠቁሟል።
ተሳታፊ ባለድርሻ አካላትም የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አንስተው በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።