News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Aug 29, 2024 489 views

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለዜጎች ሁለንተናዊ ለውጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ

33ኛው ትምህርት ጉባኤ አካል የሆነው የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ቅድመ ጉባኤ ትይዩ (የተናጥል) የዘርፎች መድረክ "የከፍተኛ ትምህርት ለከፍተኛ ለውጥ" በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል።
ነሃሴ 23/2016ዓ.ም (ትምህርት ሚኒስቴር) የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሹኔ መድረኩን በከፈቱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለዜጎች ሁለንተናዊ ለውጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ክቡር አቶ ኮራ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና ፍትሃዊነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህም ጎን ለጎን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚከናወኑ የምርምር ስራዎችም የዜጎችን ህይወት የሚያሻሽሉ ተግባራት እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት ተቋማት ምቹ የመማር ማስተማር ከባቢን መፍጠር የሚያስችል ተቋማዊ ሥርዓትና ሁኔታን መፍጠር እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚታዩ የመሠረተ ልማት ጉድለቶችን ለማሟላት የሚደረጉ ጥረቶችን በመደገፍ የድርሻውን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ ተቋማቸው (የስቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ) በ1988 ዓ.ም ስራ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ለመንግስት ሠራተኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ለሀገር እድገት ገንቢ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም ለመንግስት ግዥ ሥርዓት መዘመን፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መለወጥ፣ ለፍትህና ለዳኝነት ስርዓት መጎልበት፣ ለከተማ ልማት እና ሌሎቹም የወሳኝ መስኮች አገልግሎት መሻሻል የበኩሉን አስተዋጸኦ ማበርከቱን አመላክተዋል፡፡
ተቋሙ በአሁኑ ወቅት በ54 የትምህርት ፕሮግራሞች የሰው ሀይል ለማፍራት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ከነዚህ ፕሮግራሞች ማካከልም 91%ቱ በ2ኛ እና በ3ኛ ድግሪ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩ የትምህርት ሚኒስቴር የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃጸም ሪፖርት፣የአካዳሚክ ጉዳዮች፣ የምርምርና ጉድኝት፣የአይሲቲና ዲጂታል ትምህርት፣የአስተዳደርና መሰረተ-ልማት የሪፎርም ስራዎች አፈጻጸም ሪፖርቶች እና የኢትዮጵያ ትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን አመታዊ የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርበዋል፡፡
በተጨማሪም በወሳኝ የከፍተኛ ትምህርት የሪፎርም አጀንዳዎች ላይ ፓናልስቶች ቀርበው ሀሳባቸውንና ተሞክሮዋቸውን አካፍለዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች፣ የትምህርት ሚኒስቴር አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
Recent News
Follow Us