News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Feb 22, 2024 1.3K views

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን አሰላ ከተማ በባለሀብት ተሳትፎ ለሚገነባው አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአርሲ ዞን አሰላ ከተማ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በባለሀብት ተሳትፎ ለሚገነባው የመጀመሪያው አዳሪ ትምህርት ቤት የመሠረት ድጋይ አስቀምጠዋል ።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴን ጨምሮ የኦሮሚያ ክልል የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ቶላ በሪሶ እና ሌሎች የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ መረሃ ግብር ወቅት ደረጃቸውን የጠበቁ የትምህርት ተቋማትን መገንባት ብቁ የሆነ የሰው ኃይልን ለማፍራት የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚቻለው ትምህርትን ለሁሉም ማድረስ ሲቻል ነው ያሉት ሚኒስትሩ በገጠርም ሆነ በከተማ ሁሉም ዜጋ ጥሩ የትምህርት ዕድል እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ንቅናቄ ከተጀመረ ጀምሮ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን አንስተው ይህ ትምህርት ቤት በግለሰብ ደረጃ የሚገነባ የመጀመሪያው አዳሪ ትምህርት ቤት ነውም ብለዋል።
እንዲህ ዓይነት ትምህርት ቤቶች ጥራት ያለው ትምህርትን ለመስጠት አስተዋጽአቸው የጎላ መሆኑንም አንስተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ቶላ በሪሶ በበኩላቸውበትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ትምህርት ሚኒስቴርና ክልሉ ላደረገው ጥሪ ባለሀብቱ አቶ ተድላ ኃ/ጊዮርጊስ ለሠጡት ምላሽ አመስግነዋል።
የትምህርት ሥራ በመንግስት ብቻ የሚሠራ አይደለም ያሉት ዶ/ር ቶላ ህብረተሰቡ አሁንም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በአቶ ተድላ ኃ/ጊዮርጊስ የሚገነባው አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ሲጠናቀቅ ለአቅመ ደካማ ወላጅ አልባ ህፃናት አገልግሎት የሚሠጥ መሆኑም ተገልጿል።
በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ከተጀመረ ጀምሮ በሀገር ደረጃ እስካሁን ሦስት ሺ የሚደርሱ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች የተገነቡ ሲሆን ከ11 ሺ በላይ ትምህርት ቤቶች ደግሞ እድሳት የተደረገ ላቸው መሆኑም በመድረኩ ተገልጿል
Recent News
Follow Us