News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Oct 13, 2022 3K views

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በትናንትናዉ እለት በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ አደጋ የደረሰባቸዉን ተማሪዎች ጠየቁ

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በትናንትናዉ ዕለት አደጋ የደረሰባቸዉን በሃዋሳ ዩኒቨርስቲ የሚፈተኑ የ2014 ዓም 12ኛ ክፍል ተፈታኞች ደህንነት ለመጠየቅ ዛሬ ጠዋት ሀዋሳ ሪፌራል ሆስፒታል ተገኝተዋል፡፡
“አሁን ዋናዉ የእናንተ ማገገም ነዉ፡፡ ለፈተናዉ አትጨነቁ” በማለትም የተጎዱ ተማሪዎች በጤንነታቸዉ ዙሪያ እንዲያተኩሩ መክረዋል፡፡
በትናንትናዉ እለት ህይወቱ ላለፈዉ ተማሪም የተሰማቸዉን ከፍተኛ ሀዘን ገልጸዉ ለተማሪዉ ወላጆች እና ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡
በደረሰዉ ጉዳት እንደአገር እናዝናለን፡፡ ነገር ግን ሂደቱ የፈተና ስርዓቱ ከስርቆት ተጠብቆ ተማሪዎች በራሳቸዉ ጥረት ዉጤታማ እንዲሆኑ እና የተሻለች አገር የመገንባት በመሆኑ በዚህ ተስፋ መቁረጥ የለብንም ብለዋል፡፡ ወላጆችም ይህንን ተረድተዉ ከትምህርት ማህበረሰቡ ጋር በጋራ እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡
የተከሰተዉ የድልድይ መደርመስ አደጋ ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይሸጋገር ተማሪዎቹን ለማዳን ለተረባረቡ የጤና ተቋማት ፣ የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ እና የአካባቢዉ ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ትናንት በደረሰዉ አደጋ ምክንያት ተቋርጦ የነበረዉ ፈተና ዛሬ የተጀመረ ሲሆን ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የፈተና አሰጣጡንም ጎብኚተዋል፡፡
Recent News
Follow Us