News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Oct 13, 2022 1.7K views

ሰዎች ለሰዎች ድርጅት 16 ትምህርት ቤቶችን ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሊገነባ ነው፡፡

ሰዎች ለሰዎች ድርጅት ከትምህርት ሚኒሰቴር ጋር በመተባበር በአራት ክልሎች 16 ትምህርት ቤቶችን ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሊገነባ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከሰዎች ለሰዎች ድርጅት የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶሰባስቲያን ብራንዲስ ( ዶ/ር) ጋር ትምህርት ቤቶቹን ለመገንባት የሚደረገውን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
አስራ ስድስቱ ት/ቤቶች በአፋር፣ ሶማሌ፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሚገነቡ ሲሆን በዓመት በአማካይ ስምንት ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
የግንባታ ስራው በኦሮሚያ እና ሱማሌ ክልሎች የአዳዲስ ት/ቤቶች መገንባትን ያካተተ ሲሆን በአፋር እና አማራ ክልሎች ደግሞ ኣዳዲሰ ከሚሰሩ ት/ቤቶች በተጨማሪ በጦርነት የተጎዱ የት/ቤት ህንፃዎችን በአዲስ የመተካት ስራንም እንደሚያካትት በፊርማ ስነ-ስርአቱ ላይ ተገልጿል፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ድርጅቱ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው የወደሙ ትምህርት ቤቶችን የመገንባቱ ስራ የሁሉንም ማህበረሰብ ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል አስተዋፆውን እንዲያበረክት ጠይቀዋል፡፡
የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶሰባስቲያን ብራንዲስ(ዶ/ር) በበኩላቸው ሰዎች ለሰዎች ድርጅት የሚገነባቸው ት/ቤቶች አብዛኛዎቹ የግንባታ ግብአታቸው ከአውሮፓ የሚገቡና ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ናቸው ብለዋል፡፡
በዚህ አመት ግንባታቸው የሚጀምረው 16ቱም ት/ቤቶች ግንባታቸዉ በሁለት አመት ከሶስት ወር ተጠናቆ ለአገልግሎት የሚበቁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ሁለት አመታት በጦርነት እና ግጭት ምክንያቶች በአፋር፣ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች ከ1,336 በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ መዉደማቸዉ ይታወቃል፡፡
እነዚህን ሙሉ በሙሉ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር ባዘጋጀዉ የዲዛይን ስራ መሰረት ለመገንባት በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡
በያዝነው አመትም ስድስት ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠ ሲሆን በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ እና በሰዎች ለሰዎች ድርጅት ግንባታቸዉ ተጀምሯል፡፡
Recent News
Follow Us