News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Mar 05, 2021 271 views

ሴቶች የተሻለ ቦታ እንዲደርሱ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡

የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ፒ ኤች ዲ) ቱሉ ዲምቱ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱም በትምህርት ቤት ውስጥ እየተደረገ ስላለው የሴት ተማሪዎች ድጋፍ እና በትምህርት ቤት ውስጥ ስላለው የትምህርት አሰጣጥ ሂደት ገለፃ ተደርጓል።

በትምህርት ቤት ውስጥ ያሉትን የልዩ ፍላጎት እና የስነ ልቦና ድጋፍ መስጫ ክፍሎች ጉብኝት የተደረገ ሲሆን በባለሙያዎችም ስለሚሰጠው አገልግሎት ማብራሪያ ተሰጥቷል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በትምህርት ቤት ውስጥ የስርዐተ ፆታ ክበብ በማቋቋም ጥቃቶችን ለመከላከል እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች መሆኑን ገልፀው በቀጣይነትም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ትምህርት ቤቱ ለሴት ተማሪዎች ምቹ ሁኔታን የፈጠረ በመሆኑ ሌሎች ትምህርት ቤቶችም ይህን አርያ ሊከተሉ እንደሚገባ ፕሬዝዳንቷ ገልፀዋል።

ፕሬዝዳንቷ ሴት ልጅ የተሻለ ቦታ እንድትደርስ የሁሉም ድጋፍ ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን የነገ የበለፀገች ኢትዬጵያን ለመገንባት የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

ፕሬዝዳንቷ ሴቶች የተሻለ ቦታ እንዲደርሱ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚገባ  ገልፀው ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Recent News
Follow Us