News Detail
Mar 11, 2021
1.3K views
የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በሰላም መጠናቀቁ ተገለፀ።
የትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና መጠናቀቁን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫውም ከየካቲት 29 - መጋቢት 02 ,2013ዓ.ም ሲሰጥ የነበረው የ2012ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በሰላም መጠናቀቁን አስታውቋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ፒ ኤች ዲ) ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ የሁሉም ድርሻ ከፍተኛ እንደነበረ ገልፀው ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ ላደረጉ አካላት፣ ተማሪዎች እና ወላጆች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
እንደ ሀገር የተለያዩ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ የትምህርት ጊዜ ወደ ኋላ እንዳይቀር እና የተማሪዎች የትምህርት ዘመን እንዳይራዘም መደረጉንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በዘንድሮው የፈተና አሰጣጥ ስርቆትን ለማስቀረት 8 ፈተናዎችን በ 32 ስብጥር በማድረግ ኩረጃ እንዳይኖር መደረጉም በመግለጫው ተነስቷል።
የፀጥታ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ፈተናውን በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉንም ሚኒስትሩ በመግለጫው አንስተዋል።
የሀገር አቀፍ ፈተና ውጤቱም በቅርብ ጊዜ እንደሚገለፅ እና ተፈታኞችም በዚሁ አመት ወደ ዩኒቨርስቲ እንደሚገቡ ተገልጿል።
የ2012 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ፈተናውን ከ 358 ሺህ በላይ ተማሪዎች መውስዳቸው ተነግሯል