News Detail
Jun 03, 2025
118 views
ኩረጃን የሚጠየፍ ትውልድ ለመፍጠር እስካሁን በተወሰዱ እርምጃዎች በሁሉም ዘንድ መተማመን መፍጠር መቻሉ ተገለጸ።
የትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት ሥርዓቱ ያለውን መሰረታዊ ችግር ለመፍታት ከወሰዳቸው እርምጃዎች አንዱ የትምህርት ምዘናና የፈተና አስተዳደር ሥርዓቱን ማስተካከል እንደሆነ ይታወቃል።
በዚህ ሂደት እስካሁን የተሰሩ ሥራዎችን በማስመልከት ማብራሪያ የሰጡት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ትምህርት እውቀት ሲሆን ሰርተፊኬት ደግሞ ያንን እውቀት የምንለካበት ነው ብለዋል።
በስርቆት፣ በማጭበርበርና በኩረጃ የሚገኝ ነገር እውቀት ሳይኖር ሰርተፊኬት ማግኘት ነው ያሉት ሚኒስትሩ ይህ ደግሞ እውቀት አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን ሰርተፊኬቱ እውቀት አለህ ስለሚለው ምንም ሳያቅ ሰርተፊኬት በእጁ ስላለው ብቻ እውቀት አለኝ ብሎ የሚያምን የህብረተሰብ ክፍል ይፈጠራል፤ ይህም ህብረተሰቡን በጣም እንደሚጎዳው አብራርተዋል።
በተለይም በትምህርት ዘርፉ ተንሰራፍቶ የነበረውን ማጭበርበር፣ ስርቆትና ኩረጃ ተማሪዎች ብቻ የሚያደርጉት ቢሆን ኖሮ የልጆቹ ችግር ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። ነገር ግን ይህን የሚያደርጉት ተማሪዎች፣ የትምህርት ቤት አስተዳደሮች፣ የክልል ባለ ስልጠናት እና ሌሎችም የኛ አካባቢ ልጆች እንዲያልፉ በሚል የሚያደርጉት በመሆኑ ከፍተኛ የሞራል ውድቀት ውስጥ የተገባበት እንደነበር አንስተዋል።
በመሆኑም ወደፊት ትውልዱን በጥራት ማስተማር አለብን ካልን ከመሰረቱ ችግሩን መፍታትና በኩረጃና በማጭበርበር የሚገኝ እውቀት እንደሌለና ይህም ሀገር እንደሚጎዳ በሁሉም ዘንድ መተማመን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።
በዚህም ይህንን ስብራት ለማስተካከል በተወሰደው የለውጥ እርምጃ ተማሪዎች በትምህርት ዘርፉ በቀላሉ አጭበርብሮና ኮርጆ ማለፍ የለም የሚለውን በማወቅ በሥርዓቱ ማጥናት፣ ቤተ መጽሃፍት መግባት፣ ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀም፣ በትርፍ ጊዜያቸው ቲቶሪያል መማርና ለትምህርታቸው በቂ ትኩረት መስጠት ጀምረዋል።
መምህራንም በአግባቡ ተዘጋጅተው ማስተማርና ተማሪዎችን በሚገባ ማዘጋጀት፣ የትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራንም ሁሉም ተማሪዎች ትምህርታቸውን ተከታትለው ከክፍል ክፍል በትክክል ተመዝነው እንዲያልፉ ማድረግ የጀመሩበት፣
በየክልሉ ያለው የትምህርት መዋቅርም በኩረጃ የኔ አካባቢ ይህን ያህል አለፈ ከሚል የቁጥር ጨዋታ ወጥተው በትክክል የትምህርት ምዘና በየደረጃው በማድረግ ልጆች ባላቸው እውቀት ብቻ ተመዝነው የሚያልፉበት ሥርዓት እየፈጠሩ ይገኛል። ለአብነትም የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና በአግባቡ እየተገበሩ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ይህንን ማስቀጠል ከተቻለ የምዘናና የፈተና አስተዳደር ሥርዓቱን በሚገባ ያስተካክለዋል። የገጠመውን የሞራል ክስረት በሚገባ አስወግዶ ትምህርት በእውቀትና በችሎታ ብቻ የሚለው በጀመርነው አግባብ ወደ ኋላ ሳይመለው ማስረጽ ከቻልን ለምናደርገው የትምህርት ጥራት መሻሻል እንደ መነሻ ይሆናልም ብለዋል።
በአጠቃላይ የትምህርት ምዘናና ፈተና አስተዳደር ሥርዓቱን ማስተካከል ከተጀመረ ጀምሮ በተወሰዱ እርምጃዎች ከአሁን በኋላ በሁሉም ዘንድ ግልጽ በሆነ መንገድ በማጭበርበርና በኩረጃ የሚገኝ ነገር እንደሌለ እና ተምሮና ተግቶ በማጥናት ብቻ ውጤት እንደሚገኝ በተማሪዎችና በማህበረሰቡ ዘንድ መተማመን መፈጠሩንም ገልጸዋል።
አክለውም ዘንድሮም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተናን በተለመደው አግባብ ለመስጠት በቂ ዝግጅት መደረጉ ጠቅሰው በተለይም ከባለፈው ዓመት በተሻለ 150 ሺ የሚደርሱ ተማሪዎች ፈተናቸውን በበየነ መረብ ይወስዳሉ ብለዋል።
በዚህ ሂደት በቀጣይ ሶስት ዓመታት ሁሉም ተማሪዎች በበየነ መረብ የሚፈተኑበት ሁኔታ ይፈጠራል ያሉት ሚኒስትሩ የፈተና አስተዳደር ሥርዓቱ በዚህ መልኩ መስመር ከያዘ ብቃት ያላቸውና ተወዳድሪ የሆኑ ተማሪዎችን ለማፍራት ሌሎች የትምህርት ጥራት ሊያረጋግጡ የሚችሉ ተግባራት ላይም ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።
በዚህ ዓመት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከ600 ሺህ በላይ ተማሪዎች በወረቀትና በበየነ መረብ ፈተናቸውን ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።