News Detail
Oct 09, 2020
551 views
በመምህርነት ሲያገለግሉ የነበሩ ባለሙያዎች ሀጋራዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጅት እንዲያደርጉ ተጠየቀ
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለ7 ወራት የተቋረጠውን የመማር ማስተማር ሂደት ለማገዝ ከዚህ ቀደም በመምህርነት ሙያ ሲያገለግሉ የነበሩ መምህራን በአቅራቢያቸው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለማገልገል ዝግጅት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር መደበኛ ትምህርትን በሚያስቀጥልበት ወቅት በትምህርት ቤቶች አካላዊ እርቀትን ለማስጠበቅ የተማሪዎች ቁጥር ከ20-25 እንዲሆን መወሰኑን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች እንደየ አካባቢያቸው ሁኔታ በፈረቃ ትምህርት የሚሰጡ ይሆናል፡፡
በዚህም ወቅት በትምህርት ቤቶች የመምህራን እጥረት እንዳይኖር ለማድረግ ከዚህ ቀደም በመምህርነት ሲያገለግሉ የነበሩና የ መምህርነት ስልጠናን ወሰደው ሌላ ዘርፍ የተቀላቀሉ ባለሙያዎች በየአካባቢያቸው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተመልሰው ሃገራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ፒ ኤች ዲ) "እኔም አስተምራለው" በሚል መሪ ቃል ከ ሰኞ ጀምሮ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ከዚህ ቀደም በምህርነት ሲያገለግሉ የነበሩና በ መምህርነት ሙያ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን የመመዝገብ ስራ ይሰራል ብለዋል።
በዚህም መሰረት ባለሙያዎች በአቅራቢያቸው ባሉ ትምህርት ቤቶች በመሄድ እና በመመዝገብ የትምህርቱን ዘርፍ በሙያቸው እንዲያግዙ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።