News Detail
Dec 27, 2025
18 views
ለፌዴራል ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የወደፊቱ አገር ተረካቢዎች ሁለንተናዊ ሰብዕና የሚገነባባቸው ተቋማት መሆናቸው ተመላከተ፤ የቦንጋ ፌዴራል ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በአዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ ላይ የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሹኔ እንደገለጹት አዳሪ ትምህርት ቤቶች የነገዎቹ አገር ተረካቢዎች ሁለንተናዊ ስብዕና የሚገነባባቸው ቦታዎች ናቸው።
ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ጥራት ያለው ትምህርት ከማቅረብ ጎን ለጎን በጥሩ ባህሪ የተገነቡ ፣ሥነምግባር የተላበሱና በሙያቸው የላቀ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ዜጎች የሚፈሩባቸው ማዕከላት መሆናቸውንም ክቡር አቶ ኮራ አስገንዝበዋል።
የትምህርት ቤቶች ትኩረት በአብዛኛው የአካዳሚክ ዕውቀትን በማስተላለፍ ላይ ያተኮረ መሆኑን የጠቀሱት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ከንድፈ ሀሳብ እውቀት ባሻገር የተማሩትን ወደ ተግባር በመለወጥ የማህበረሰቡን ችግር መፍታት የሚችሉ ዜጎችን ማፍራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
በልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች መማር ያለባቸው ለዕውቀት ብቻ ሳይሆን ያወቁትን ወደ ተግባር ለመቀየር፣ ለመለወጥ፣ ከሌላው ጋር አብሮ መኖር የመሳሰሉ የትምህርት ምሶሶዎችን በማሟላት ሙሉ ሰው መሆን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
የቦንጋ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎችም በትምህርት ቤቱ በሚኖራቸው ቆይታ በመቻቻል ፣በመከባበር፣በመዋደድና አብሮ በመኖር ምሳሌ ሊሆኑ እንደሚገባም ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ደስታ ገነሜ በበኩላቸው የትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት ስርዓቱ ላይ ያሉ ችግሮችን በመፍታት የነገ አገር ተረካቢዎችን ለማፍራት በልዩ ሁኔታ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ከልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱ መምህራንና አስተዳደር ሠራተኞች ፣ከተማሪዎች ከክልሉና ዞኑ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮዎች እንዲሁም ከቦንጋ ዩኒቨርስቲ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።
በመጨረሻም የትምህርት ቤቱን የመማሪያ ክፍሎች በመጎብኘትና አሻራቸውን በማኖር ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀዋል።