News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Sep 25, 2025 37 views

በትምህርት ሪፎርሙ የትምህርት ምዘናና ፈተና አስተዳደር ሥርዓቱን ለማስተካከል የተወሰዱ እርምጃዎች እና ከታች ጀምሮ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ዋና ዋና ስራዎች

በሀገራችን የትምህርት ምዘናና ፈተና አስተዳደር ሥርዓቱን ለማስተካከል ከተወሰዱት እርምጃዎች አንዱ በትምህርት ፖሊሲው የተቀመጠውን አንድ ተማሪ ወደ ሚቀጥለው ክፍል ወይም እርከን ለመሸጋገር ቢያን 50 ከመቶና በላይ አማካይ ውጤት ማስመስመዝገብ አለበት በሚል የተደነገገውን የማስጠበቅ ጉዳይ ነው። በዚህም በሪፎርሙ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎችም ይሁኑ በየትኛውም የትምህርት ደረጃ ያሉ ተማሪዎች 50 በመቶና በላይ አማካይ ውጤት ሲያመጡ ወደ ሚቀጥለው ክፍል/እርከን እንዲሸጋገሩ እየተደረገ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር ተማሪዎች 50 ከመቶ በታች አማካይ ውጤት አምጥተው ወደ ሚቀጥለው ክፍል እንዲዛወዱ ወይም በቀጥታ ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ ይደረግ እንደነበር የሚታወስ ነው። አሁን ባለው አሰራር ይህንን ሙሉ በሙሉ በማስቀረት በየትኛውም የክፍል ደረጃ 50 በመቶና በላይ አማካይ ውጤት ያላመጣ ተማሪ ወደ ቀጣዩ ክፍል ወይም እርከን አይዛወርም።
በተጨማሪም በአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ መሰረት በ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና እንዲሰጥ የተደረገ ሲሆን በሁሉም ክልልና ከተማ አስተዳደሮች በነዚህ ፈተናዎች 50 በመቶና በላይ አማካይ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ወደ ቀጣዩ ክፍል እንዲዛወሩ እየተደረገ ይገኛል። ይህም በየደረጃው የትምህርት ጥራቱ ያለበትን ደረጃ እየለኩ ለመሄድ ትልቅ አስተዋጻኦ ይኖረዋል።
በተመሳሳይ ባለፉት አራት ዓመታት የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኞች 50 ከመቶና በላይ አማካይ ውጤት ያመጡ ወደ ዩኒቨርሲቲ በቀጥታ እንዲገቡ እየተደረገ ሲሆን በአንድ በኩል የትምህርት ፖሊሲውን እያሰጠበቅን በሌላ በኩል ደግሞ የተወሰነ ድጋፍ ተደርጎላቸው ውጤት ማምጣት ለሚችሉ ተማሪዎች አዲስ የሪሚዲያል ፕሮግራም ተቀርጾ ተማሪዎች ለአንድ ዓመት በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድርግ በቀጣዩ ዓመት ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ በማድረግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛል። ይህ አካሄድም በሂደት 50 በመቶና በላይ አማካይ ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ በሪሚድያል የሚገባው ተማሪ ቁጥር እየቀነሰ ሄዶ ፕሮግራሙ የሚጠፋበት ሁኔታ ይፈጠራል።
ሌላው በፈተና አስተዳደር ሥርዓቱ የተወሰደው እርምጃ የፈተና ኩረጃና ስርቆትን በማስቀረት ፈተናውን መስጠት መቻሉ ነው። ከዚህ ቀደም በነበረው ኩረጃ እንደ ስኬት የሚቆጠርበት፣ ተማሪዎች ተደራጅተው ፈተና የሚሰሩበት፣ የሚኮርጁበት ፣ ኩረጃ በተቋም ደረጃ ጭምር የሚበረታታበት እና ከፍተኛ የሞራል ውድቀት የነበረበትን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ በማስቀረት ትምህርት በእውቀትና በራስ ጥረት ብቻ የሚለውን በማህበረሰቡ ዘንድ ማስረጽ የተቻለበት ሁኔታን መፍጠር ተችሏል። ይህም በሂደት በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ስነ ምግባር የተላበሱ እውቀትና ብቃት ያላቸውን ዜጎች ለማፍራት ያስችላል።
በሌላ በኩል የትምህርት ጥራትን ከታች ጀምሮ ለማረጋገጥ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾ ወደ ትግበራ ተገብቷል፤ የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ለማሻሻል በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ሀብት በማሰባሰብ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ሥራ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፤ መንግስት ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ልዩ ትኩረት በመስጠት በርካታ አዳዲስ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው በርካታ ህጻናት በቅድመ መደበኛ ትምህርት እንዲያልፉ እየተደረገ ይገኛል፤ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ለመምህራና ትምህርት ቤት አመራሮች እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የአጠቃላይ ትምህርት አዋጅም ጸድቆ ወደ ተግባር እንዲገባም ተደርጓል።
በተጨማሪም ተማሪዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የማንበብ ባህላቸው እያደገና ለትምህርታቸው የሚሰጡት ትኩረት እየጨመረ መጥቷል። መምህራናና የትምህርት ቤት አመራሮች የማጠናከሪያ ትምህርት በልዩ ትኩረት እየሰጡ ሲሆን ወላጆችም የልጆቻቸውን ትምህርት መከታተል ጀምረዋል።
በአጠቃላይ በትምህርቱ ዘርፍ የተጀመረውን ሪፎርም የበለጠ በማጠናከር ፍትሃዊና ጥራት ያለው ትምህርትን ለዜጎች በማድረስ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ልጆችን ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል።
ፍትሃዊና ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም
ትምህርት ሚኒስቴር
Recent News
Follow Us