News Detail
Aug 29, 2025
143 views
የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ስልጠና መምህራን የሚያስተምሩትን የትምህርት ዓይነት ይዘት በአግባቡ እንዲያውቁና እንዴት ማስተማር እንደሚችሉ ግንዛቤ የተፈጠረበት እንደነበር ተጠቆመ፤ ለሁለተኛ ደረጃ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ሲሰጥ የቆየው የክረምት ልዩ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ተጠናቋል፡፡
የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ንጋቱ (ዶ/ር) እንደገለጹት ከሐምሌ 28/2017 እስከ ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም ለመምህራንና የት/ቤት አመራሮች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና መምህራን የሚያስተምሩትን የትምህርት ዓይነት ይዘት በአግባቡ እንዲያውቁና ለተማሪዎችም እንዴት ማስተማር እንደሚችሉ ግንዛቤ የተፈጠረበት ነበር ብለዋል፡፡
በስልጠናው መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮቹ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት ኖሯቸው ማስተማር እንዲችሉ ፣ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ተግዳሮቶችንም ተቋቁመው የመማር ማስተማር ስራን እንዴት መምራት እንዳለባቸው አቅም የገነቡበት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ሰልጣኝ መምህራኑ የወሰዱት የማስተማር ስነ ዘዴ ስልጠናም ወቅታዊ ችግሮችን ለመፍታትም ሆነ እየተተገበረ የሚገኘውን ስርኣተ ትምህርት በአግባቡ መተግበርና መፈጸም እንደሚያስችላቸውም ዶ/ር ሙሉቀን አብራርተዋል።
የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማትና አስተዳደር ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ አሰገደች መሬሳ በበኩላቸው ከሐምሌ 27 እስከ ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም ከ60 እስከ 120 ሰዓት በሶስት ተከፍሎ በተሰጠው የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ስልጠና 64 ሺ 900 መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮችን ተካፋይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በስልጠናው ከ2 ሺ 400 በላይ የሚሆኑ አሰልጣኖችም መሳተፋቸውንና 184 ሺ የስልጠና ሞጁሎች ተዘጋጅተው መሰራጨታቸውን የዴስክ ኃላፊዋ ወ/ሮ አሰገደች ተናግረዋል፡፡
ሰልጣኞቹ የድህረ ስልጠና ምዘና ፈተና በበይነ መረብ መውሰዳቸውን ጠቁመው በቀጣይ ቀናት ውስጥ የይለፍ ቃል /Password/ እና የመጠቀሚያ ስማቸውን/Username/በመጠቀም ውጤታቸውን ማየትና ከ70 በመቶ ውጤት ያመጡ ሰልጣኞችም የምስክር ወረቀታቸውንም አውርደው መውሰድ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
በመጨረሻም ሃላፊዋ ለዚህ የመምህራንና የት/ቤት ስልጠና መሳካት አስተዋዕኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
Recent News
Sep 02, 2025
Aug 29, 2025
Aug 28, 2025
Aug 23, 2025