News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Feb 17, 2025 65 views

ቼክ ሪፐብሊክ በትምህርቱ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር እንደምትፈልግ ተገለጸ። የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ የተመራ ልዑካን ቡድን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይታቸው የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለዜጎች ጥራት ያለው ትምህርትን በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ የለውጥ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑንና በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በርካታ የሪፎርም ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ለልዑካን ቡድኑ አብራርተዋል።
ትምህርትን ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራ እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ በዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነጻና በራሳቸው የሚያስቡ እንዲሆኑ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአቅም ግንባታ፣ በነጻ የትምህርት እድል፣ በመምህራን ልውውጥ እንዲሁም በስፖርትና ኪነ-ጥበብ ትምህርት ዘርፍ የትብብር መስኮችን ማሳደግ ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተም አብራርተውላቸዋል፡፡
የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ በበኩላቸው ቼክ ሪፕብሊክና ኢትዮጵያ በትምህርቱ ዘርፍ የረጅም ጊዜ ግኙነት እንዳላቸው አንስተው ይህንን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከፋይናንስ ድጋፍ ባሻገር በነጻ የትምህርት እድል፣ በመምህራን ልውውጥ፣ በጥናትና ምርምር፣ በሳይንስ፣ በስፖርትና ኪነ-ጥበብ ትምህርት በመሳሰሉት ዘርፎች ላይ የበለጠ ለመስራትና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ሁለቱ አካላት ግንኙነታቸውን የበለጠ በሚያጠናክሩባቸው ሌሎች ጉዳዮች ላይም ሰፊ ውይይቶችን አድርገዋል።
Recent News
Follow Us