News Detail
Nov 20, 2024
114 views
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በብቃት ላይ የተመሠረተ አመራር እንዲኖር እየተሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስታወቁ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴርና የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በስምምነቱ ወቅት እንደገለጹት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአመራሮች ምደባ ብቃትን መሰረት ያደረገ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአንድ አገር ልማትና ስኬት የሚወሰነው በዋነኛነት በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች ላይ በሚያገለግሉ አመራሮች ብቃት መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
ከአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድም ውጤታማ አመራርን ለማፍራትም ሆነ ሀብትን በውጤታማነትና በአግባቡ ለመጠቀም ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ጠቅሰዋል፡
የአፍሪከ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው ጠንካራ አመራር ለመፍጠር ግልጽ የአመራር ልማት ፖሊሲ፣ በስልጠናው የሚለይ የአመራር ልማት ፕሮግራም እንዲሁም ሳይንሳዊ የአመራር ምዘና ስርዓት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ዛሬ የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተሟላ ብቃት ያለውና ቁርጠኛ አመራር በመፍጠር የተጀመሩ የሪፎርምና የለውጥ ስራዎች በታሰበው መንገድ ለውጤት እንዲበቁና ስኬተማ እንዲሆኑ እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡
ደረጃውን የጠበቀ አገር በቀል ስልጠና መኖሩ አገሪቱ የምትፈልገውን አመራር በብዛትና በብቃት ለማፍራት ከማሰቻሉም ባሻገር አመራሮችን በውጭ አገር በማሰልጠን የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ ለማስቀረት እንደሚያግዝም አቶ ዛዲግ አብራርተዋል፡፡
የስምምነት ሰነዱን ትምህርት ሚኒስቴርን በመወከል የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ እንዲሁም የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚን በመወከል ደግሞ የአካዳሚው ምክትል ርእሰ አካዳሚ ወ/ሮ መሠረት ደስታ ፈርመዋል፡፡