News Detail
Nov 19, 2024
85 views
ሀንጋሪ ከኢትዮጵያ ጋር በትምህርት ዘርፍ ያላትን የትብብር ግንኙነት ለማሳደግ እየሰራች መሆኑ ተጠቆመ።
የሀንጋሪ ሪፐብሊክና የኢፌዲሪ የትምህርት ሚኒስቴር ለመቶ ኢትዮጵያውያን ነጻ የትምህርት እድል የሚያስገኝ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርተ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ ስምምነቱን በተፈራረሙበት ወቅት እንደገለጹት ሀንጋሪ ከኢትዮጵያ ጋር ባላት የረጅም ጊዜ ታረካዊ ግንኙነት በትምህርቱ መስክ በቅድመ ምረቃ፣ በድህረ ምረቃ እና በፒ ኤች ዲ መርሐ-ግብሮች ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ነጻ የትምህርት እድል ስትሰጥ መቆየቷን አመልክተዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል በተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት መሰረትም አገሪቱ በየዓመቱ ለ100 ኢትዮጵያውያን ነጻ የትምህርት እድል ለመስጠት መዘጋጀቷንና ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የትምህርትና የዩኒቨርስቲ ለዩኒቨርስቲ ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሀንጋሪ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚስተር አቲላ ኮፓኒ በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል በትምህርት ዘርፍ የቆየ የትብብርና የወዳጅነት ግንኙነት መኖሩን ጠቁመው በትምህርቱ ዘርፍ ዛሬ የተፈረመው ስምምነት የሁለቱን አገራት ግንኙነትን ይበልጥ እንደሚያጎለብተው ተናግረዋል፡፡
ሀንጋሪ ለኢትዮጵያ ነጻ የትምህርት እድል ስትሰጥ የመጀመሪያ አለመሆኑን የጠቆሙት አምባሳደሩ ዛሬ በተፈረመው የስምምነት ሰነድ ዋነኛ ኣላማም ሀገሪቱ እ. ኤ. አ. ከ2017 ጀምሮ ለ50 ተማሪዎች በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ስትሰጥ የነበረውን ነጻ የትምህርት እድል እ.አ.አ. ከ2025 ጀምሮ ወደ 100 ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሀገሪቱ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ነጻ የትምህርት እድል በእጥፍ ለማሳደግ የወሰነችው የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እ.ኤ.አ. በ2023 በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ መሆኑንም አምባሳደር አቲላ ኮፓኒ ጨምረው አብራርተዋል፡፡
በመግባቢያ ስምምነት ሰነዱ የፊርማ ስነ ስርዓት ላይም የሁለቱም ወገኖች የሚመከታቸው የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡