News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Sep 01, 2024 1.5K views

የትምህርት ጥራትና የፍትሃዊነት ችግሮችን በጥልቅ ሪፎርም ለመፍታት እየተካሄደ ለሚገኘው የለውጥ ስራ ስኬት በጋራና በትብብር መስራት እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) አስገነዘቡ

የትምህርት ሚኒስትሩ ክቡር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በ33ኛው ትምህርት ጉባኤ ማጠናቀቂያ ላይ እንደገለጹት የትምህርት ጥራትና ፍትሃዊነት እንዲረጋገጥ የትምህርት ሴክተሩን በሪፎርም መለወጥ የምርጫ ጉዳይ አይደለም ብለዋል ።
የትምህርት ስርዓቱን ችግሮች በጥልቀት ለመፍታት ለተጀመሩ የሪፎርምና የለውጥ ስራዎች ስኬታማነት በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻዎች ከባድ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ፕሮፌሰር ብርሃኑ አስገንዝበዋል፡።
የትምህርት ዘርፉን በሪፎርም በመለወጥ በፍጥነት እየተቀየረ ያለውን ዓለም ተቋቁሞ አገርን ሊያስቀጥል የሚችል ትውልድ ማፍራት እንደሚገባም ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል።
የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው ተማሪዎች ከታችኛው እርከን ጀምረው የሥነ ምግባር ትምህርት እየተማሩ በመሆኑ ጥሩ ስነ ምግባር የተላበሱና ምክንያታዊ እንዲሆኑ ተደጋግፎ መሥራት ይገባል ብለዋል።
የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ከመግባታቸው በፊት ከቴክኖሎጂ ጋር እንዲተዋወቁ በስርዓተ ትምህርቱ የኮምፒውተር ትምህርት እንዲማሩ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የክልል እና የከተማ መስተዳድሮች ለመምህራን ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ለትምህርት ልማት ስኬታማነት የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡም ክብርት ወ/ሮ አየለች ጠይቀዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሹኔ በዚሁ ጊዜ ሲናገሩ የዩኒቨርስቲ መምህራን በተቀራራቢ የብቃት ደረጃና የማስተማር ችሎታ ላይ እንዲደርሱ በቀጣይ ተከታታይነት የአቅም ግንባታ ስራዎችን መሥራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ቅድመ ምሩቃ የመውጫ ፈተና ከሌሎች ተማሪዎች እኩል እንዲበቁ ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አቶ ኮራ አመልክተዋል።
ለ3 ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው 33ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤም በአገር አቀፍ ፈተና ስኬታማ ስራዎች ላከናወኑ የፌደራልና የክልል ባለድርሻዎች ዕውቅና በመስጠትና ባለ 12 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።
Recent News
Follow Us