News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Aug 28, 2024 1.3K views

የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር እና የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በትምህርት ተቋማት ስፖርት ልማት ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የመግባቢያ ስምምነቱን በተፈራረሙበት ወቅት ስፖርት አእምሮአዊና አካላዊ ብቃት የተላበሱ ዜጎችን ለማፍራት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የትምህርት ሚኒስቴር ብቃት ያላቸው ዜጎችን የማፍራት ተግባር የትምህርት ዘርፉ ሪፎርም አካል አድርጎ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በዚህም መሠረት በቀጣዩ የትምህርት ዘመን የትምህርት ቤቶች ስፖርት ውድድርን ለማካሄድ እና መርሃ ግብሩን አጠናክሮ ለማስቀጠል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው በሁሉም ዘርፍ አሸናፊ አገር ለመፍጠር ብቁና ንቁ ዜጎች ማፍራት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው በማህበረሰብ አቀፍ እና በባህላዊ ስፖርቶች ላይ የትምህርት ማህበረሰቡን በማሳተፍ በጋራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ ተቋማት በዕለቱ የተፈረረሙት የመግባቢያ ሰነድ መሰረት በቀጣይ በየደረጃው ባሉ ቴክኒካል ባለሙያዎች በየጊዜው እየታቀደ እና እየዳበረ ለተሻለ ስኬት እንደሚውል ጠቁመዋል፡፡
የትብብር ስምምንቱ ዓላማ በሁለቱ ተቋማት መካከል ወጥ እና ተከታታይነት ያለው ቅንጅታዊ አሰራርን በመፍጠር የትምህርት ቤት ስፖርት ልማትን በማስፋፋት የስፖርት ትምህርት ጥራትን ለማሻሻል መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ሰፖርታዊ ልማትን ባህል ያደረገ በመማር ውጤቱ የተሻለ የሆነ ንቁና ሁለንተናዊ ሰብዕናው የተሟላ ተተኪ ትውልድ ለማፍራት ምቹ ሁኔታን መፍጠር የስምምነት ሰነዱ ሌለው ዓላማ መሆኑን ተመላክቷል፡፡
Recent News
Follow Us