News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Jan 26, 2023 3.8K views

“መጪውን ትውልድ ጠቃሚ በሚሆንበት መልክ እና ደረጃ ኮትኩቶ በማሳደግ ለሀገር አገልግሎት በማብቃት ረገድ የምሁራን ሚና ወሳኝ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጥር 16/2015 ዓም.(ትምህርት ሚኒስቴር) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት፣ “መጪውን ትውልድ ጠቃሚ በሚሆንበት መልክ እና ደረጃ ኮትኩቶ በማሳደግ ለሀገር አገልግሎት በማብቃት ረገድ የምሁራን ሚና ወሳኝ ነው” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመላው ሀገሪቱ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከተውጣጡ የዩኒቨርስቲ ምሁራን ጋር ‘ለሀገር ብልጽገና፤ የምሁራን ሚና’ በሚል ርዕስ ውይይት አድርገዋል።
ተሳታፊዎች በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ እንዲሁም በሀገራዊ ልማት፣ ሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፤ ሰፊ ውይይትም ተደርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ምሁራን በተሻለ ደረጃ እንድትገኝ የሚመኟትን ሀገር ለመገንባት አስፈላጊውን ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ገለፀዋል።
ኢትዮጵያ እያጋጠሟት ያሉትን የተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን በመገንዘብ ፍላጎቶቻቸውን ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በማጣጣም እና የበሰሉ መፍትሔዎችን በማፍለቅ የበለጠ ሚና እንዲጫወቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚሁ ወቅት አሳስበዋል።
ሁሉም የዩኒቨርሲቲ ምሁራን በዚህ ኃላፊነት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀው፣ ለሀገራዊ ፈተናዎች ተጨባጭ መፍትሔዎችን ለማምጣት ይቻል ዘንድ እውነተኛ ምሁራዊነትን መተግበር ከምሁራኖቻችን እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
በተሳታፊዎች የተነሡ አንኳር ጉዳዮችን በተመለከተም የሚመለከታቸው አካላት ክትትል እንዲያደርጉ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
Recent News
Follow Us