News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Feb 02, 2021 553 views

ሀገር አቀፍ የ“እንድናገለግልዎ ማስክ ያድርጉ” ንቅናቄ በትምህርት ቤቶች በይፋ ተጀመረ።

"የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዳይቋረጥ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዬን እጠቀማለሁ" በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ የ“እንድናገለግልዎ ማስክ ያድርጉ” ንቅናቄ በትምህርት ቤቶች በይፋ ተጀምሯል።

ንቅናቄውን የትምህርት ሚኒስቴር ከጤና ሚኒስቴር ፣ ከህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት እንዲሁም ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር አዘጋጅተውታል።

በፕሮግራሙ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር ፣ የጤና ሚኒስቴር፣የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት  እንዲሁም የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አመራሮችና ባለሙያዎች   በዳግማዊ ሚኒሊክ መሰናዶ ትምህርት ቤት  በመገኘት  ንቅናቄውን በይፋ አስጀምረዋል።

ንቅናቄው ከዛሬ ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል። የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ዳኛው ገብሩ የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዳይቋረጥ እና ትምህርት ቤቶች እንዳይዘጉ በትምህርት ቤት ውስጥ እና ከትምህርት ቤት ውጪ ተማሪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛን በአግባቡ ሊጠቀሙ ይገባል ብለዋል።

ከዛሬ ጀምሮም በትምህርት ቤቶች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛን ማድረግ ልምድ ሊሆን እንደሚገባው በፕሮግሩሙ ላይ ተገልጿል።

የትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ ወ/ሮ ሐረጓ ማሞ በበኩላቸው በህብረተሰቡ ውስጥ መዘናጋት እየተስተዋለ እና የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየተስፋፋ በመሆኑ ሁሉም አካል የኮቪድ መከላከያዎችን በአግባቡ ሊጠቀም ይገባል ብለዋል። በቀጣይም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሲመጡ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛቸውን በአግባቡ እንዲያደርጉና ሌሎች የኮቪድ መከላከያዎችን እንዲተግብሩ የትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ ወ/ሮ ሐረጓ ማሞ ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህ ቀደም የትምህርት ሚኒስቴር ኮቪድን ለመከላከል የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛዎችን ለትምህርት ቤቶች ማሰራጨቱ ይታወሳል።

Recent News
Follow Us