News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Aug 11, 2020 1.3K views

ለ12ኛ ክፍል አይነ ስውራን ተማሪዎች እየተሰጠ ያለው የተስማሚ ቴክኖሎጂ ስልጠና በታሰበለት ደረጃ እየሄደ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የ12ኛ ክፍል ፈተናን ሁሉም አይነሰውራን ተማሪዎች በኦንላይን እንዲፈተኑ ለማድረግ በሙሉ አቅም እየተሰራ መሆኑን አስታወቋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሁሪያ ዓሊ ተማሪዎቹ ፈተናውን በኦንላይን ለመፈተን የሚያስችላቸውን መሰረታዊ እውቀት እየያዙ መሆኑን ተናግረዋል።

ገና ስልጠናው ሳይጀመር ለፈተና ብቁ ሊሆኑ አይችሉም ብሎ መገመት ለተማሪዎቹ ዝቅ ያለ ግምት መስጠት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ በተቻለ መጠን ለፈተና ዝግጁ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

እንደ አስፈላጊነቱ አጋዥ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎችም ለመመደብ እቅድ መያዙን አብራርተዋል።

ተማሪዎቹ እንደየ አካባቢያቸው ሁኔታ ከዚህ ቀደም የኮምፒውተር እውቀት ያላቸውና የሌላቸው በመሆናቸው ተመሳሳይ አቀባበል የላቸውም ያሉት የተስማሚ ቴክኖሎጂ ለአይነስውራን በኢትዮጵያ ዳይሬክተርና አሰልጣኝ ታምሩ እውነቱ (ዶ/ር) ይህንን ታሳቢ በማድረግ ተማሪዎችን በመለየት ለፈተና ዝግጁ ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል።

ተማሪዎቹ በበኩላቸው አብዛኞቻችን ከዚህ ቀደም የኮምፒውተር እውቀት ስለሌለን የስልጠናው ጊዜ ቢራዘም የሚል ጥያቄ አንስተዋል።

ከመላ ሃገሪቱ የተውጣጡ 250 ዓይነስውራን ተማሪዎች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተስማሚ ቴክኖሎጂ ስልጠና እየወሰዱ ነው።

ስልጠናው ለፈተና ዝግጁ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ለሚኖራቸው የስራ ጊዜ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል።

Recent News
Follow Us