News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Aug 01, 2025 66 views

የትምህርት ሚኒስትሩ በጣሊያን ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት የተማራ ልዑካን ቡድን አባላትን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ ።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፊሰር ብርሃኑ ነጋ በጣሊያን ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት Lia QUARTAPELLE PROCOPIA የተመራ ልዑካን ቡድን አባላትን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በዚሁ ጊዜ ሚኒስትሩ በአገሪቱ ትምህርትን በጥራትና በፍትሃዊነት ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ እየተከናወኑ ስለሚገኙ የሪፎርም ተግባራት ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡
በቀደመው ጊዜ ትምህርትን የማስፋፋትና ተደራሽ የማድረግ ሰፊ ሥራ ቢሰራም የትምህርት ጥራት ተዘንግቶ መቆየቱን ጠቅሰው ይህንንም ከመሰረቱ ለመፍታት በትምህርት ዘርፉ የተለያዩ የሪፎርም ተግባራት ተቀርጸው እየተተገበሩ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም በትምህርት ስርዓቱ የተበላሸውን የሞራል መሰረት ለማስተካከል ሥርዓተ ትምህርቱን ከመቀየር ጀምሮ የፈተና አስተዳደር ስረዓቱን ከስርቆትና ኩረጃ በጸዳ መልኩ በመስጠት የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
ስታንዳርዳቸውን ያሟሉ ትምህርት ቤቶች በጣም ጥቂት መሆናቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሩ በትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማት ማሻሻል ንቅናቄ ከ17 ሺ በላይ ትምህርት ቤቶችን መገንባትና ማደስ መቻሉንም አንስተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የተማሪ መጽሃፍትን በሁለተኛ ደረጃ አንድ ለአንድ ማድረስ መቻሉንና ከአለም አቀፍ ትብብር ለትምህርት በተገኘ ድጋፍ ተጨማሪ መጽሃፍትን ለአንደኛ ደረጃ ለማሳተምና ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን አብራርተው የጣሊያን መንግስት ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የጣሊያን የምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት Lia QUARTAPELLE PROCOPIA በበኩላቸው ጣሊያን በኢትዮጵያና በአፍሪካ በተለያዩ የልማት መስኮች ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን አንስተው በቀጣይ የዓለም አቀፉ ትብብር ለትምህርት (GPE) መሪነት እንደምትረከብና በዘርፉ ድጋፍ ማድረግ ፍላጎት እንዳላትም ገልጸዋል።
አክለውም ኢትዮጵያ በትምህርቱ ዘርፍ እየወሰደቻቸው ያሉ ሪፎርሞችን በአድናቆት እንደሚመለከቱት ገጸው ለተጀመሩ የሪፎርም ተግባራት ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ እደሚያደርጉ ተናግረዋል።
Recent News
Follow Us