News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Jul 17, 2025 392 views

የትምህርት ሚኒስቴር የሚያስገነባቸውን የፌዴራል አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች በ2018 የትምህርት ዘመን ስራ ለማስጀመር እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ።

በአዲሱ የትምህርት ዘመን ትምህርት ሚኒስቴር እያስገነባቸው ካሉ ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል የተወሰኑት በመጪው የትምህርት ዘመን ስራ እንደሚጀምሩ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞ በሰጡት ማብራሪያ እንዳስታወቁት በሳይንስና በቴክኖሎጂ የበቁ የነገ የዚች ሀገር መሪ መሆን የሚችሉ ዜጎችን ለማፍራት የፌዴራል ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የፌዴራል ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶቹ ከሁሉም አካባበዎች የሚመጡ ተማሪዎች የሚማሩባቸው፣ አብሮ መኖርና ማደግን የሚለምዱባቸውና የአገሪቱ የወደፊት መሪዎችን የምናፈራባቸው ቦታዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡
በዚህም መነሻ የትምህርት ሚኒስቴር በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች እያስገነባቸው ካሉ ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ድረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል የተወሰኑትን በመጪው የትምህርት ዘመን ስራ ለማስጀመር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ ከአርባ የማያንሱ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተሰጡ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናዎች ከሞላ ጎደል ሁሉም ተማሪዎችን ማሳለፍ መቻላቸውንም በአብነት አንስተዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር አዲስ በተገነቡት የፌዴራል ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በ2017 የትምህርት ዘመን 8ኛ ክፍል ካጠናቀቁ ተማሪዎች መካከል መልምሎ ለማስገባት ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ሲሆን ለዚህም ተማሪዎች ተገቢውን መስፈርት አሟልተው እንዲጠባበቁ ማስታወቂያ ማውጣቱ ይታወሳል።
Recent News
Follow Us