News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Jun 13, 2025 13 views

የመንግስት ትምህርት ቤቶች ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚገባባቸው ምቹ ተቋማት እንዲሆኑ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ የትምህርት ሚኒስትሩ ገለፁ።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዱራሜ ከተማ የሚገነባው ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተጀምሯል።
በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በየአካባቢው መሠረተ ልማት የተሟላላቸው ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ብቃት ያላቸውና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ለማፍራት እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።
እንደ ሀገር ከድህነት ለመውጣት ትምህርት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል፤ ለዚህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል እድል አግኝቶ የሚማርበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ግዴታ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለይም በተፈጥሮ ያለ የኢኮኖሚ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ በትምህርት ግን በሀብታምና ድሃ መካከል ምንም ልዩነት ሊኖር አይገባም ያሉት ሚኒስትሩ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚማርበትን የመንግስት ትምህርት ቤት ተመራጭና ምቹ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የመንግስት ትምህርት ቤቶች ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚማርባቸው ተቋማት መሆን አለባቸው፤ ለዚህም አዲስ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ዲዛይን ተሠርቶ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቅሰው ነገ የኢትዮጵያ መሪ የሚሆኑ ልጆችን ለማፍራት የሚያስችሉ ትምህርት ቤቶችን እየገነባን እንገኛለን ያሉ ሲሆን፣
ትምህርት ሚኒስቴር በመላ ሀገሪቱ በቂ መሰረተ ልማት የተሟላላቸው 51 የሚደርሱ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለመገንባት አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ በበኩላቸው የትምህርት ሥርዓቱን በሁሉም ዘርፍ ለማስተካከል በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለይም በክልሉ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች በመሆናቸው እንዲህ ዓይነት ሞዴል ትምህርት ቤቶች መገንባት ትርጉሙ ብዙነው ያሉ ሲሆን ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ይህ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ 509 ሚሊየን ብር እንደሚፈጅና ሙሉ ወጪ በትምህርት ሚኒስቴር እንደሚሸፈንም በመድረኩ ተገልጿል።
የትምህርት ቤቱ ግንባታም በአንድ ዓመት ጊዜ ተጠናቆ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲጀምር በትምህርት ሚኒስቴርና በክልሉ ትምህርት ቢሮ መካከል ሥምምነት ተፈርሟል
Recent News
Follow Us