News Detail
Dec 07, 2024
211 views
የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎትን ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ።
በትምህርት ሥርዓቱ የሚስተዋለውን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት ችግር ለመቅረፍ በሚቻልበ ጉዳይ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
በምክክር መድረኩ የተገኙት የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት ላይ የሚስተዋለውን ችግር መቅረፍ ካልተቻለ የሚፈለገውን የትምህርት ጥራት ማረጋገጥና አለም አቀፍ ተወዳደሪ የሆኑ ተማሪዎችን ማፍራት እንደማይቻል ጠቅሰው ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩርት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በተለይም ተማሪዎች የሚማሩትን ትምህርት በአግባቡ እንዲረዱና ውጤታማ እንዲሆኑ እንግሊዝኛ ቋንቋን የማንበብ፣ የመጻፍ፣ የመናገርና የማዳመጥ ክህሎታቸውን በሚገባ ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
የቀጣዩ ትውልድ እጣ ፈንታ የሚወሰነው አሁን በሚሰራው ሥራ መሆኑን በመገንዘብ የመማር ማስተማር ሥነ - ዘዴውን ማስተካከል እንዲሁም ተማሪዎች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበትን ምቹ ሁኔታ በትምህርት ቤቶች መፍጠር ይገባልም ብለዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራር ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ንጋቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው የእንግሊዝኛ ቋንቋ በትምህርት ዓይነትና በማስተማሪያ ቋንቋነት በትምህርት ሥርዓቱ እየተሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሰው ነገር ግን ከፍተኛ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት ችግር መኖሩን የሚያመላክቱ ጥናቶችን አቅርበዋል።
በዚህም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት ችግር በተማሪዎችና በመምህራን ዘንድ እንደሚስተዋል አንስተው ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ትምህርት ቤትን መሰረት ያደረገ ሥልት ቀይሶ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ትምህርት ሚኒስቴርም https://learn-english.moe.gov.et የተሰኘ ያለ ምንም የኢንተርኔት ክፍያ የሚሰራ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ፓርታል አልምቶ ወደ ሥራ ማስገባቱን የጠቀሱት መሪ ሥራ አስፈጻሚው ይህንን ፖርታል ተማሪዎች፣ መምህራን እንዲሁም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎታቸውን ማሳደግ የሚፈልጉ ዜጎች እንዲጠቀሙበት በሚገባ በማስተዋወቅ ረገድ ሚድያዎችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመድረኩም የተለያዩ ጽሁፎች ቀረበው በተሳታፊዎች ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ተሳታፊዎችም ተማሪዎች በክፍል ውስጥና ከክፍል ውጪ ቋንቋውን እንዲጠቀሙበት እና ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ የሚያበረታታ ሁኔታ አለማኖሩ ችግሩን የጎላ እንዳደረገው ገልጸው ይህንን ለመፍታት መምህራንና ተማሪዎች በድፍረት ቋንቋውን እንዲጠቅሙና ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ የሚያደርጉ ስልቶችን መቀየስ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በመጨረሻም የቋንቋ ክህሎትን በማሳደግ ረገድ የተሰሩ ሥራዎችና ሥልቶችን መሰረት በማድረግ ተሞክሮዎች መቀመርና ማስፋት በተለይም ክልል ከክልል፣ ትምህርት ቤት ከትምህርት ቤት ልምድ የሚለዋውጡበት ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባም ተመላክቷል።
በምክክር መድርኩ ከሁሉም ክልልና ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የመጡ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
Recent News
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምግብ ሜኑ ተመሳሳይ እንዲሆን ተወሰነ።
Dec 09, 2024
የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎትን ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ።
Dec 07, 2024