News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Nov 30, 2024 249 views

በኢትዮጵያና በፈረንሳይ መንግስታት መካከል በትምህርት መስክ ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን የፈረንሳይ እና የአውሮፓ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን ኖኤል ባሮት አስታወቁ፡፡

ሁለቱ አገሮች በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት አስር በመቶ ነጻ የትምህርት እድል የሚያስገኝ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን ኖኤል ባሮት ከትምህርት ሚኒሰትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር የስምምነት ሰነድ በተፈራረሙበት ወቅት እንደገለጹት እ.ኤ.አ. በ1947 የተመሰረተው የሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት በኢትዮጵያና በፈረንሳይ መካከል በትምህርት መስክ ያለው የቆየ ወዳጅነትና ትብብር ማሳያ ነው፡፡
የሊሴ ገ/ማርያም ትምህርት ቤት በ77 ዓመታት ታሪኩ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ማሰልጠኑን የገለጹት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተፈረመው ስምምነትም በሁለቱ አገራት መካከል በትምህርት መስክ ያለውን መተማመንና ትብብር ከፍ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡
ስምምነቱ እውን እንዲሆን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ላደረጉት ትጋትና አስተዋጽኦም የፈረንሳዩ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው ትምህርትን በጥራትና በፍትሀዊነት ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በስምምነቱ መሠረት በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ከፍለው መማር ከማይችሉ ቤተሰቦች የሚገኙ ተማሪዎችን በመለየት እስከ አስር በመቶ የሚደርስ ነጻ የትምህርት እድል እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ እንደ ሊሴ ገ/ማርያም ባሉ ትምህርት ቤቶች ከፍለው ማስተማር የማይችሉ ቤተሰቦችን ልጆች ተቀብለው ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ይህም የበለጠ ዴሞክራሲያዊ እና የተረጋጋ ማህበረሰብን ለመፍጠር እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያና በፈረንሳይ መካከል በሊሴ ገ/ማርያም ትምህርት ቤት አማካኝነት ጠንካራ ወዳጅነትና የትብብር ግንኙነት መኖሩን የጠቆሙት ሚኒስትሩ ሰምምነቱ የነበረውን ወዳጅነትና ትብብር የበለጠ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል፡፡
ከመግባቢያ ስምምነቱ አስቀድሞም የፈረንሳይና አውሮፓ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን ኖኤል ባሮት እና የኢፌዲሪ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በትምህርት ቤቱ ተዘዋውረው ጉብኝት አድርገዋል፡፡
በስምምነቱ ወቅት የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስተር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ እና በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሚስተር አሌክሲስ ማሌክን ጨምሮ ሌሎችም የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
Recent News
Follow Us