News Detail
Apr 15, 2024
1K views
የጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት ፕሮግራም የዜጎችን የትምህርት ጥያቄ በፍጥነት እየመለሰ እንደሆነ ተገለጸ
በኦሮሚያ ብ/ክ/መንግስት በአዳማ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት መደበኛ ያልሆን ትምህርት የስራ ሂደት ባለቤት አቶ አቡ ነጋሽ በቦኩ ክ/ከተማ የዳቤ ቆጬ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት የጎልማሶች መማሪያ ማዕከልን ባስጎበኙበት ወቅት የጎልማሶች መሰረታዊ ትምሀርት ፕሮግራም ውጤቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚታይ ሁለንተናዊ ፋይዳ ያለው የሰው ሀይል ልማት ስራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ አቡ በአሁኑ ወቅት በአዳማ ከተማ አስተዳድር ስር 18 ማዕከላት መኖራቸውን ጠቅሰው በማዕከላቱም 21 አመቻቾችና 2,305 ጎልማሶች በመማር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እንደ ሃላፊው ገለጻ የከተማ መስተዳድሩ በቅርቡ ባካሄደው ሪፎርም 24 የገጠር ቀበሌዎችንና ከ40 በላይ ት/ቤቶችን ወደ ራሱ እንዳካተተ ጠቅሰው እነዚህን ሰፊ የህብረተሰብ ክፍል ለማስተማር እንዲቻል በቀጣይ የአመቻቾችን ብዛት ወደ 89 ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የትምህርት ቤቱ ሪዕሰ መምህር አቶ ያሚ ደሜ በበኩላቸው በዚህ አመት በማዕከሉ 67 ጎልማሶች በመማር ላይ ያሉ መሆኑንና ከክልል በወረደው የስራ አፈጻጸም ግምገማ መመሪያ መሰረት የጎልማሶች ማዕከል ባለባቸው ት/ቤቶች ላይ የአመራሮች የአፈጻጸም ግምገማ ይህንን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነም ገልጸው ይሄም ለስራው ትኩረት እንዲሰጥ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ጠቁመዋል።
በማስተማር ስራ ላይ ያገኘናቸው አመቻች መምህርት ኦላንቱ መሓመድ እንደገለጹት ደግሞ ጎልማሶችን አሳምኖ ወደ ማዕከሉ ማምጣት ከባድ ቢሆንም መጥተው ፊደልና ቁጥርን መለየት ከጀመሩ በኋለ የትምህርት ፍላጎታቸውና አቀባበላቸው በዚያው ልክ እየጨመረ እንደሚሄድ ጠቅሰው ለማሳያነትም ጥቂት የማይባሉ ጎልማሶች በአመት መማር የሚጠበቅባቸውን ትምህርት በግማሽ አመቱ ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡
በማዕከሉ በመማር ላይ ያገኘናቸው ወ/ሮ ደሪቡ ህንሰርሙ ወደ ማዕከሉ ከመምጣታቸው በፊት ምንም ያልተማሩ ሲሆኑ አመቻቻቸው ቤት ለቤትና በስራ ቦታቸው ጭምር በመሄድ ባደረጉት ተደጋጋሚ የማሳመን ስራ ወደ ማዕከሉ መምጣታቸውን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት ማንበብ፣ መጻፍና ማስላት መቻላቸን ገልጸዋል።
Recent News
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምግብ ሜኑ ተመሳሳይ እንዲሆን ተወሰነ።
Dec 09, 2024
የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎትን ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ።
Dec 07, 2024