ዜና

በግጭት ለተፈናቀሉ ሴት ተማሪዎች ድጋፍ ተደረገ

በተለየ ሁኔታ ድጋፍ ተደርጎላቸው 12ኛ ክፍልን ያጠናቀቁ ሴት ተማሪዎችም በአሶሳ ዩኒቨርስቲ ግቢ ተመርቀዋል።

ህዳር 17/2015ዓም . (ትምህርት ሚኒስቴር) በቤኒሻንጉል ክልል በግጭት ለተፈናቀሉ ሴት ተማሪዎች 11 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የሚያወጡ የመማሪያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረጓል።
ለክልሉ ትምህርት ቢሮ ድጋፉን ያስረከበው ኩሶ ኢንተርናሽናል ዩ ገርልስ 2 ፕሮጀክት የተባለ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው ።
ኩሶ ኢንተርናሽናል ለሁለት ዓመት በተለየ ሁኔታ ድጋፍ ሲያደርግላቸው የነበሩና 12ኛ ክፍልን ያጠናቀቁ 131 ሴት ተማሪዎችንም በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ግቢ አስመርቋል።
ድርጅቱ ሴት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ድጋፍ እያደረገ ሲሆን ቀደም ሲልም ለ250 የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንም የሳይኮ ሶሻል ስልጠና መሥጠቱም ተገልጿል ።
በአሁኑ ድጋፍም 6,500 ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያገኙና ከ4,500 በላይ የሚሆኑ ሴቶችና እናቶችም የንፅህና መጠበቂያ እንደተዘጋጀላቸው ተገልጿል ።
በመድረኩ የተገኙት የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ አማካሪ አቶ የሰውዘር በላይነህ ሴቶችን ማስተማር ልማት የተረጋገጠባት ሀገር ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን ገልፀው ሴት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡና ውጤታማ እንዲሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የቤኒሻንጉል ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጃፋር ሀሩን በበኩላቸው ለድጋፉ አመስግነው የቁሳቁስ ልገሳው ሴት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ በማድረግ የመማር ማስተማር ስራውን እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ተመራቂ ተማሪዎቹ ከመደበኛው ትምህርት ጎን ለጎን የህይወት ክህሎት፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፣ የስራ እድል ፈጠራ እንዲሁም የአይ ሲቲ ስልጠና በተለያየ ጊዜ የተሰጣቸው መሆኑ ተገልጿል ።
ተመራቂ ተማሪዎቹ በበኩላቸው ድርጅቱ ያደረገላቸው ድጋፍና ስልጠና ከፍተኛ ህልምና በራስ መተማመን እንዲኖራቸው እንዳደረጋቸው ገልፀው ጠንክረው እንደሚማሩ ተናግረዋል።
ኩሶ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በክልሉ እየሰራ ያለውን ስራ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም የማስፋት እቅድ እንዳለው በመድረኩ ተገልጿል ።