ዜና

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንድቀጥል ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከሃገር አቀፍ ፈተናዎች አገልግሎት የሥራ ሀላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ገልፀው፤ ውጤታማነቱ ቀጣይነት እንዲኖረው  ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል። 

በመድረኩ ላይ የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና አሰጣጥ ዝግጅት፣ የዩኒቨርስቲ ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና አሰጣጥ፣ የትምህርት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ተቋማዊ ሪፎርም፣ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ (autonomous) ለማድረግ ስለተያዘው ዕቅድ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዋናነት ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድን ከመገንባት አኳያ በትምህርት ሚኒስቴር የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራና ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ስለመኖራቸውም ተብራርቷል።
ቋሚ ኮሚቴው የ2014 ዓ/ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናን በሚመለከት ከወላጆች የሚነሱ ስጋቶችን እና ጥያቄዎችን እንዲሁም፤ ከየክልሉ ትምህርት ቢሮዎች ያሰባሰባቸውን መረጃዎች መሰረት ላነሳቸው ጥያቄዎች ፤ በስራ ኃላፊዎቹ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡  
ምንጭ  :-  (ኢ.አ.ድ