ዜና

በጦርነት አካባቢ ሲያስተምሩ ለነበሩ መምህራን የስነ ልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

ትምህርት ሚኒስቴር ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር በጦርነቱ አካባቢ ለነበሩ መምህራን የስነ ልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ /psychosocial) ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።

ስልጠናው መምህራኑ ከስነ ልቦና ጫና ተላቀው ውጤታማ የመማር ማስተማር ስራ ለመስራት የሚያስችል ነው ተብሏል።
የትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና የትምህርት አመራር የሙያ ፈቃድ ዳይሬክተር ወ/ሮ ካሳነሽ አለሙ ይህ ስልጠና መምህራን በጦርነት ከደረሰባቸው የስነ ልቦና ጫና ተላቀው የመማር ማስተማር ስራ ውጤታማ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።
ሰልጣኞችም ከስልጠናው በኋላ በየትምህርት ቤቶቻቸው የተማሪዎችን ስነ ልቦና ወደ ነበረበት ለመመለስ ጥረት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ስልጣኞች ከስልጠናው በኋላ በየ ዞናቸው ሄደው የአሰልጣኞች ስልጠና እንደሚሰጡም ተገልጿል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ መኳንንት አደመ በበኩላቸው ስልጠናው በጦርነት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ መገንባት ብቻ ሳይሆን የደረሰውን ስነልቦናዊ ጉዳት ለማከም ከፍተኛ አስተዋፆኦ አለው ብለዋል።
ስልጠናውም በክልሉ በሁለት ማእከላት በባህርዳርና ደብረ ብርሃን ከተሞች እንደሚሰጥ ገልፀዋል።
ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ስልጠና ለ3,500 መምህራን መሰጠቱም ተገልጿል።