ትምህርት ልማት ዘርፍ

የትምህርት ልማት ዘርፍ

የአጠቃላይ ትምህርት ዋና ዓላማ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ 12ኛ ክፍል፤ የጐልማሶች ትምህርትና ሥልጠናን ጨምሮ ለዜጐች ጥራት ያለው ትምህርት በመደበኛና መደበኛ ባልሆነ መልኩ በመስጠት ለሥራና ለከፍተኛ ትምህርት ማዘጋጀት ነው። ይህን ዓላማ ለማሳካት የአጠቃላይ ትምህርት በአራት ዘርፎች የተደራጀ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የትምህርት ልማት ዘርፍ ነው።

 

የትምህርት ልማት ዘርፍ በሚኒስቴር ዴኤታ የሚመራ ሲሆን ለዜጐች ጥራትና አግባብነት ያለው ትምህርት ለመስጠት እንዲቻል የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ፣ የመምህራንና ትምህርት አመራር ልማትና አስተዳደር እና የሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች ማሻሻያ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል።

 

ሥርዓተ ትምህርት በትምህርትና ስልጠና ሥርዓት ውስጥ የሚገኙ መርሃ ግብሮችን የሚመራ ቁልፍ መሳሪያ ነው። ሥራዎቹም በሁለት ዋና ዋና ከፍሎች የተከፈለ ነው። እነሱም የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ እንዲሁም የትምህርት ሥርዓቱን ሊያጎለብቱ የሚችሉ ጥናትና ምርምሮችን ማካሄድ ናቸው። የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ አገራዊ የሥርዓተ ትምህርት ማእቀፍ ላይ በመመስረት የይዘት ፍሰት፣ አጥጋቢ የመማር ብቃት እና መርሃ ትምህርት የሚያዘጋጅ ሲሆን በተጨማሪም በየትምህርት ዓይነቱ የተማሪ መፃህፍት፣ የመምህሩ መምሪያና ተጨማሪ መፃህፍት ዝግጅት፣ ህትመትና ስርጭትን ያካትታል። በሌላ በኩል የሥርዓተ ትምህርት ጥናትና ምርምር በሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት፣ ትግበራና ድህረ ትግበራ ወቅት ያለውን ጥራት፣ አግባብነት፣ ብቃትና ውጤታማነት ማረጋገጥ የሚያስችል መረጃ በመሰብሰብና በመተንተን የሚያካሄድ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የአገር በቀል እውቀትን፣ ክህሎትንና ልምዶችን በትምህርት ለማሳደግና ለማበልፀግ ጥልቀት ያለው ጥናትና ምርምር በማካሄድ በሚዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርት እንዲካተት ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም በተዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን መንስኤ በጥናት በመለየትና የመፍትሄ ምክረ ሃሳብ በማመንጨት ሥርዓተ ትምህርቱን ለማሻሻል ይሰራል።

 

የመምህራንና ትምህርት አመራር ልማት ሁለት ዋና ዋና የስራ ዘርፎችን አጣምሮ የያዘ ሲሆን የመምህራን ልማትና አስተዳደር የመምህራንና የመምህራን አሰልጣኞች ምልመላና ስምሪትን ለማሳለጥ የተዘጋጁ ፖሊሲዎች፣ ስታንዳርዶችን እና የብቃት ማዕቀፎች መሠረት በማድረግ የመምህራን ምልመላና አስተዳዳር መመሪያዎች፣ ማኑዋሎች ያዘጋጃል፤ ለትግበራ የሚረዱ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ይሰጣል፣ አተገባበሩን ከክልሎች ጋር  በመተባበር ይከታተላል፡፡ ተከታታይ የስራ ላይ ሙያ ማሻሻያ ሥልጠናዎችን ይሰጣል፡፡ በሌላ በኩል የትምህርት አመራር ልማትና አስተዳደር የትምህርት አመራሩን ምልመላና  ስምሪት ለመምራት የሚያስችሉ መመሪያዎችና ማኑዋሎች ስታንዳርድና የብቃት ማእቀፎችን ያዘጋጃል፤ ለትግበራ የሚረዱ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ይሰጣል፣ አተገባበሩን ከክልሎች ጋር  በመተባበር ይከታተላል። ተከታታይ የስራ ላይ ሙያ ማሻሻያ ስልጠናዎችን ይሰጣል።

 

የሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገትን በማስመዝገብ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ትምህርቶች ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ለእነዚህ የትምህርት አይነቶች ትኩረት በመስጠት የመማር ማስተማሩን ሂደት በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ስታንዳርዳቸውን የጠበቁ የስልጠና ማቴሪያሎችን የማዘጋጀት፣ ወጥ የሆኑ የቤተ ሙከራ ናሙናዎችን የማዘጋጀት፣ የአኒሜሽን ቡድን በማደራጀት ክልሎችን የመደገፍ፣ የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ ክፍተቶችን መሰረት ያደረገ የመምህራንን አቅም የመገንባት እና የፈጠራ ስራ እንዲጎለብት  የማበረታታት ስራዎች ይከናወናሉ፡፡

 

በትምህርት ልማት ዘርፍ ስር የተደራጁት ጄኔራል ዳይሬክቶሬቶች አደረጃጀት፣ የተቋቋሙበት ዓላማና የሚያከናውኗቸው ዋና ዋና ተግባራት ቀጥሎ ቀርቧል።

 

  1. የስርአተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ጄኔራል ዳይሬክቶሬት
    • አደረጃጀት

የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ጄኔራል ዳይሬክቶሬት በስሩ ሦሥት ዳይሬክቶሬቶችን ይዞ የተደራጀ ሲሆን እነሱም የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ፣ የሥርዓተ ትምህርት ጥናትና ምርምር እና የግብረገብና የዜግነት ትምህርት  ዳይሬክቶሬቶች ናቸው፡፡

    • ዓላማ

የኅብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ፍላጎቶች መሠረት ያደረገ እና ዓለም አቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ ሥርዓተ ትምህርት በመቅረፅ የመማር ማስተማሩን ክንውን ስኬታማ ማድረግ ነው።

    • ዋና ዋና ተግባራት
      • በሃገራዊ የትምህርት ብቃት ማዕቀፍና የሥርዓተ-ትምህርት ማዕቀፍ መሠረት የይዘት ፍሰት፣ አጥጋቢ የመማር ብቃት እና መርሃ ትምህርት እንዲሁም የተማሪ መፃህፍት፣ የመምህሩ መምሪያና ተጨማሪ መፃህፍት አዘጋጅቶ ስራ ላይ እንዲውል ያደርጋል።
      • የሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና ማሻሻል የሚመራበት ሃገራዊ የፖሊሲና የስትራቴጂ ሃሳቦችን ያመነጫል፤ በሚወሰነው መሠረትም የማሻሻያ ሥራዎችን ይሠራል፤ ይተግብራል፣ አፈጻጸሙን ይከታተላል፣ ይገመግማል።
      • የሥርዓተ-ትምህርት ጥናትና ምርምር ከፌደራል እስከ ትምህርት ተቋማት ድረስ የሚመራበትን የፖሊሲና የስትራቴጂ ሃሳቦችን ያመነጫል፤ ፈጻሚዎችን ያበቃል፣ ሀገራዊ የትምህርት ጥናትና ምርምር ውጤቶች ቋት በማደራጀት ያሰባስባል።
      • የሁለተኛ ደረጃ ዝርዝር ሥርዓተ-ትምህርት፣ መፃህፍት ዝግጅትና ማሻሻል ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ይሰራል።
      • በሥርአተ-ትምህርት ዝግጅትና ማሻሻል የክልሎችን አቅም ይገነባል።
      • የተማሪ፣ የመምህሩ መምሪያ እና የደጋፊ መጻህፍት ዝግጅትና ማሻሻል ሃገራዊ ፖሊሲ፣ ስትራቴጅ፣ መመሪያና መርሃ ሀሳብ ያዘጋጃል፤ ሥራ ላይ እንዲውል ያደርጋል።
      • ሥርዓተ-ትምህርቱ በቴክኖሎጂ ተደግፎ የሚሰጥበትን እንዲሁም ዲጂታል በማድረግ ለሁሉም ተማሪ ተደራሽ የሚሆንበትን ሥርዓት በመዘርጋት ተፈፃሚ ያደርጋል።

 

  1. የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማትና አስተዳደር ጄኔራል ዳይሬክቶሬት
    • አደረጃጀት

የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማትና አስተዳደር ጄኔራል ዳይሬክቶሬት በስሩ ሶስት ዳይሬክተሬቶችን ይዞ የተደራጀ ሲሆን እነሱም የመምህራን ልማትና አስተዳደር የትም/ አመራር ልማትና አስተዳደር እና የአፍ መፍቻና የእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ልማት ዳይሬክቶሬቶች ናቸው፡፡

    • ዓላማ

ፍላጐትና መልካም ሥነ-ምግባር ያላቸው ወጣቶችን በመመልመል፤ ለየደረጃው የሚፈለገውን አካዳሚያዊ፣ ሙያዊና የማስተማር ሥነ-ዘዴ ብቃት የተላበሱ መምህራንን ማፍራት እንዲሁም በሁሉም እርከኖች ሙያዊ  ብቃትን ያማከለ የትምህርት አመራርና አስተዳደር  እንዲኖር ማድረግ ነው።

    • ዋና ዋና ተግባራት
      • የመምህራን፣ የትምህርት ባለሙያዎች እና የትምህርት አመራር ሀገራዊ የብቃት ማእቀፍ አዘጋጅቶ ሥራ ላይ ያውላል።
      • የመምህራን፣ የመምህራን አሠልጣኞች እና የትምህርት አመራር አስተዳደር የሚመራበት የፖሊሲ ሃሳብ ያመነጫል፤ የጥቅማጥቅም ፓኬጅ እና የትግበራ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ሥራ ላይ እንዲውል ያደርጋል፤ ትግበራውን ይከታተላል፤ ይመራል።
      • በመምህራን፣ የመምህራን አሠልጣኞችና አመራሮች ልማትና አስተዳደር ዙሪያ አዲስ ለሚቀርጹ ፖሊሲዎች፣ ስታንደርዶች፣ ማእቀፎች፣ አሠራሮች፣ መመሪያዎች፣ መርሃ ሃሳቦች እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ይሰጣል።
      • በትምህርት ሴክተሩ የመምህራን፣ የባለሙያዎችና የትምህርት አመራር እውቅና አሰጣጥ ፖሊሲ፣ ስትራትጂ፣ የአሠራር መመሪያና መርሃ ሃሳብ ዓለም ዓቀፍ ተሞክሮን በመቀመር ያዘጋጃል፤ ይተገብራል።
      • በልሕቀት ማዕከልነት የተመረጡ ተቋማት በተዘጋጁ ስታንደርዶች መሠረት መደራጀታቸውን እንዲሁም የሚመሩበትን የአሠራር መመሪያ ያዘጋጃል፤ ሥራ ላይ መዋሉንም ይከታተላል።
      • በሁሉም የአጠቃላይ ትምህርት እርከኖች የሚያስተምሩ መምህራን ለሚያስተምሩበት ደረጃ በቂ የትምህርት ዝግጅትና ብቃት እንዲኖራቸው አማራጭ የሥልጠና ሞዳሊቲዎችን በማዘጋጀት ተግባራዊ ያደርጋል።
      • በፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ላይ የተመሰረቱ የሥልጠና መርሀ ግብሮችን በማዘጋጀትና ምቹ የሥልጠና ሞዳሊቲዎችን በመጠቀም የትምህርት ቤት አመራሮችን አቅም ያጎለብታል።
      • ለመምህራን ማሰልጠኛ ተቋማት ተገቢውን ሙያዊ ድጋፍ ያደርጋል።

 

  1. የሂሳብና ሳይንስ የትምህርት ቴክኖሎጂ ማሻሻያ ማዕከል
    • አደረጃጀት

የሂሳብና ሳይንስ የትምህርት ቴክኖሎጂ ማሻሻያ ማዕከል ጄኔራል ዳይሬክቶሬት በስሩ አራት ዳይሬክተሬቶችን ይዞ የተደራጀ ሲሆን እነሱም የሂሳብ፣ የፊዚክስ፣ የኬሚስትሪ እና የባዮሎጂ ትምህርት ቴክኖሎጂ ማሻሻያ ማእከል ዳይሬክቶሬቶች ናቸው።

    • ዓላማ

በሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት ከፍ በማድረግ የተማሪዎች የሳይንስ፣ የቴክኖሎጅ፣ ኢንጂነሪነግ፣ ስነጥበብና የሂሳብ ትምህርት (STEAM) የመማር እድገትን ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀና ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊ እድገትና ትራንስፎርሜሽን መሰረት የሆነ የሳይንስና የሂሳብ እውቀትና ክህሎት በሚፈለገው ደረጃ እንዲቀስሙ በማድረግና የመማር ውጤታቸውን በማሻሻል ለሳይንስና ቴክኖሎጂ መስፋፋትና መስረፅ መሰረት መጣል ነው።

    • ዋና ዋና ተግባራት
      • የሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች ማሻሻያ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ ያደርጋል፣ ስራ ላይ ያውላል።
      • የሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች በቴክኖሎጂ ተደግፈው እንዲሰጡ የተለያዩ ስልቶችን በመቀየስ ተግባራዊ ያደርጋል።
      • የሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች የመማር ማስተማር ሂደት ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችሉ ስታንዳርዳቸውን የጠበቁ የስልጠና ማቴሪያሎችን በማዘጋጀት ተግባራዊ ያደርጋል።
      • የቤተ ሙከራ ናሙናዎችን /ሲሙሌሽን/ በማዘጋጀት እንዲሁም የአኒሜሽን ቡድን በማደራጀት ክልሎችንና ትምህርት ቤቶችን ይደግፋል።
      • በሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች የፈጠራ ስራዎች እንዲጎለብቱ የተለያዩ ስልቶችን በመቀየስ ተግባራዊ ያደርጋል፤ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል።
      • የሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ ትምህርቶቹ እየተጠናከሩ የሚሰጡበትንና ተማሪውም ፈጣሪና ተመራማሪ እንዲሆን የሚያስችሉ ስልቶችን በመቀየስ እንዲተገበር ያደርጋል፤ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል።
      • መምህራን ከአዳዲስ የማስተማር ዘዴዎች ጋር እንዲተዋወቁ የአቅም ግንባታ ስራዎች ተቋማዊ በሆነ መልኩ የሚሰጡበትን ስልቶች ተግባራዊ ያደርጋል፤ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል።
      • የሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶችን በተመለከተ የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ ክፍተቶችን መሰረት ያደረገ ሰፊ የሂሳብና ሳይንስ መምህራንን አቅም የመገንባት ስራዎች ይሰራል።
      • በሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የሚያስችሉ ጥናቶችን በማጥናት ተግባራዊ ይደርጋል።
      • ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የኢንጂነሪንግ፣ የስነጥበብና የሂሳብ(STEAM) ትምህርት ተጠናክረው እንዲሰጡ ይሰራል።
      • ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የትምህርት አውደጥናቶችን በማዘጋጀት ትምህርታዊ ጥናቶች እንዲቀርቡ በማድረግ በልምድ ልውውጥ የትምህርት አሰጣጥ ችግሮቸን ይፈታል፣ ያሻሽላል።