NEWS

ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ማሻሻያ ማዕከላትን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ::

ህዳር 12/2015ዓም. (ትምህርት ሚኒስቴር) የትምህርት ሚኒስቴር ከአሜሪካ ኢምባሲ ጋር በመተባበር ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ለተውጣጡ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ማሻሻያ ማዕከላት አስተባባሪዎች ስልጠና እየሰጠ ነው::

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚካሄደውን የእንግሊዘኛ ቋንቋ መማር ማስተማር ሂደት ማጠናከር አላማው አድርጎ የተዘጋጀው የሶስት ቀናት ስልጠናን በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር የሆኑት ትሬሲ አን ጃኮብሰን እና የትምህርት ሚኒስቴር አስተዳደርና መሰረተ ልማት ግንባታ መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ዶ/ር ሰለሞን አብርሃ በይፋ አስጀምረዋል::
አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን ስልጠናውን አስመልከቶ ባደረጉት ንግግር የእንግሊዘኛ ቋንቋ በአለም አቀፍም ይሁን በኢትዮጵያ ነባራዊ የትምህርት እና መረጃ ሰርዓት ሚናው የጎላ በመሆኑ በተለያዩ የትብብር ፕሮግራሞችና በጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ተጠናክሮ ሊሰጥ እንደሚገባው ጠቁመዋል::
ለዚህም መሳካት በኢምባሲው በኩል በጎ ፈቃደኛ መምህራን እንዲመጡ በማድረግ፣ የተለያዩ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ማሻሻያ ፕሮግራሞችን በማስቀጠልና በመቅረጽ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ገልጸዋል::
የትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደርና መሰረተ ልማት ግንባታ መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሰለሞን አብርሃ በበኩላቸው በመማር ማስተማር ሂደት ወስጥ የተማሪዎች እና የመምህራን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ መሠል ስልጠናዎች ፋይዳቸው የጎላ ነው ብለዋል::
መሪ ስራ አስፈጻሚው ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባነሱዋቸው ሃሳቦች የትምህርት ሚኒስቴር በዋነኝነት እየተገበራቸው ከሚገኙ የሪፎርም ስራዎች መካከል የተማሪዎችና መምህራንን የእንግሊዘኛ ቋንቋ ክህሎትን ማሳደግ መሆኑን ያመላከቱ ሲሆን ለተግባራዊነቱም የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አብራርተዋል::
ዶ/ር ሰለሞን በመጨረሻም ለስልጠናው መሳካት የአሜሪካን ኢምባሲ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና በማቅረብ ስልጣኞች በሚኖራቸው ቆይታ ሁሉ ተገቢውን ክሕሎት በመቅሰም ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የማጋራትና የማሳወቅ ሃላፊነትና አደራ እንዳለባቸው አሳስበዋል::