NEWS

የ12ኛ ክፍል ፈተና በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የምስጋና እና እውቅና ፕሮግራም ተካሄደ።

ትምህርት ሚኒስቴር የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የእውቅናና ምስጋና ፕሮግራም አካሂዷል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በሁለት ዙር የተሰጠው የሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ ፈተና በታቀደው መሰረት መሰጠቱን እና የነበረው ሂደትም ውጤታማ እንደነበር ገልፀው ለዚህ ስኬታማነት የበኩላቸውን ለተወጡ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የፀጥታ አካላትና አመራሮቹ በተናበበ መንገድ ለዚህ ስኬት ላደረጉት ድጋፍ እንዲሁም የዩኒቨርስቲ አመራሮች፣ መምህራንና የክልል ትምህርት ቢሮ አመራሮችን በትምህርት ሚኒስትር ስም አመሥግነዋል ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የትራንስፓርት ሚኒስቴር እና የክልል ትራንስፖርት ቢሮዎችም ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የ2014 ፈተና አሰጣጥ በትምህርት ስርዓቱ ላይ ያለውን ስብራት ለማከም ትምህርት የተወሰደበትና ተግዳሮቶችን ወደ አቅም ለመቀየር እድል የሰጠም እንደነበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገልፀዋል።
ስርቆትንና ኩረጃን የሚጠየፍ ትውልድ ለመፍጠር የትምህርት ምዘና ስርዓቱ ላይ የተጀመረ ሪፎርም አሁንም ያሉ ክፍተቶችን በማረም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል።
የትምህርት ማህበረሰቡም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ፕሮፌሰር ብርሃኑ ጠይቀዋል ።
የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና በሁለት ዙር በዩኒቨርስቲዎች የተሰጠ ሲሆን ከ900ሺህ በላይ ተፈታኞች ፈተናውን መውሰዳቸውናፈተናውን ለማስፈፀምም ከ32 ሺህ በላይ ፈተና አስፈፃሚዎች እና የፀጥታ አካላት ተሰማርተው እንደነበርም ይታወሳል።