NEWS

የ9ኛ እና 10ኛ ክፍል አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የሙከራ ትግበራ በቀጣይ አመት እንደሚጀምር ተገለፀ።

የ9ኛ እና 10ኛ ክፍል አዲሱ ሥርዓተ-ትምህርት የሙከራ ትግበራ ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ መስተዳድሮች በተመረጡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በ2015 ዓ.ም ይጀምራል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ የሙከራ ትግበራ ከሚካሄድባቸው ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ መምህራን ስርዓተ ትምህርቱን የማስተዋወቅ የአሰልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

አዲሱ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት በርካታ ደረጃዎችን አልፎ ለሙከራ ትግበራ የደረሰ መሆኑን የስርዓተ ትምህርት ማበልፀጊያ መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ቴዎድሮስ ሸዋርገጥ ገልፀዋል ።

በስርዓተ ትምህርት ዝግጅቱ ላይ የተመረጡ የመማር ማስተማር  የልህቀት ማዕከላት ዩኒቨርሲቲዎች እና ካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ በአማካሪነት እንደተሳተፉበት ሥራ አስፈፃሚው ገልፀዋል ።

የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች ስርዓተ ትምህርት ዴስክ ኃላፊ  ዛፉ አብርሃ በበኩላቸው ይህ ሥርዓተ ትምህርት ሀገር በቀል እውቀትን፣ ግብረ ገብነትን ፣ ሳይንስና  ቴክኖሎጂን የተላበሰ እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል ።

በመሆኑም በዚህ የሙከራ ትግበራ ወቅት ከመምህራንና ከባለድርሻ አካላት ብዙ ግብዓቶች እንደሚሰበሰቡ ጠቅሰው ወላጆችና ሌሎችም አስተያየት እዲሰጡበት በድረ ገፅ ይለቀቃል ብለዋል።

በሙከራ ትግበራው ወቅት የሚመጡ አስተያየቶች ተካተው በ2016 ወደ ሙሉ ትግበራ እንደሚገባም በመድረኩ ተገልጿል ።

የሚሰጠው ስልጠናም መምህራን የመምህሩን መምሪያና የተማሪውን መጽሐፉ እዲተዋወቁ ይረዳቸዋል ተብሏል ።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በ2014 የሙከራ ትግበራ ተካሂዶ በ2015 ዓ.ም  ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚደረግ ይታወቃል።